በብሔራዊ ባንክ ተመን የአንድ ግራም ወርቅ ዋጋ ስንት ደረሰ?
ባንኩ ባለ 24 ካራት 1 ግራም ወርቅ 80.7334 ዶላር (9 ሺህ 336 ብር) እየገዛ ነው
ብሄራዊ ባንክ በማዕከልና ክልል ቅርንጫፎች የሚገዛውን ወርቅ በተመለከተ የዋጋ ማሻሻያ መመሪያ አውጥቷል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ስርአት መከተል ከጀመረች በኋላ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ የሚገዛው በአለምአቀፍ እለታዊ ዋጋ መሆኑን መግለጹ ይታወቃል።
በዚህም ባንኩ እለታዊ የወርቅ መግዣ ዋጋ በድረ ገጹ ይፋ እያደረገ ይገኛል።
ብሄራዊ ባንክ የዛሬ የነሃሴ 22 2016 የወርቅ መግዣ ዋጋን ይፋ ሲያደርግ ባለ 24 ካራት 1 ግራም ወርቅ 80.7334 የአሜሪካ ዶላር ወይም በእለቱ የብሄራዊ ባንክ የምንዛሬ ዋጋ 9 ሺህ 336 ብር እየገዛ መሆኑ ተመላክቷል።
ባለ 23 ካራት 1 ግራም ወርቅ 77.3695 የአሜሪካ ዶላር ወይም በእለቱ የብሄራዊ ባንክ የምንዛሬ ዋጋ 8 ሺህ 947 ብር እየገዛ መሆኑንም ነው ያስታወቀው።
ባለ 22 ካራት 1 ግራም ወርቅ ደግሞ በ74.0056 ዶላር (8 ሺህ 558 ብር) እየገዛ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያወጣውን እለታዊ የወርቅ መግዣ ዋጋ በቀጣዩ ሰንጠረዥ ይመልከቱ፦
በተያያዘ ብሄራዊ ባንክ በማዕከልና ክልል ቅርንጫፎች የሚገዛውን ወርቅ በተመለከተ የዋጋ ማሻሻያ መመሪያ አውጥቷል።
መመሪያው ወርቅ አቅራቢ ማህበራትና ግለሰቦች ላቀረቡት ወርቅ 95 በመቶ ክፍያ በቅድሚያ በመውሰድ ቀሪውን 5 በመቶ የዋጋ መጠባበቂያ በማድረግ ወርቁን ለግዥ ማዕከላት ካስረከቡበት ቀን ጀምሮ በ30 ተከታታይ ቀናት ከተመዘገበው ዋጋ መርጠው በሚያቀርቡት መሰረት ክፍያ ያገኛሉ ይላል።
ትላልቅ አምራቾች ወይም ኩባንያዎች ከወርቅ ሽያጭ ከሚያገኙት ገቢ 50 በመቶ በውጭ ምንዛሬ ለራሳቸው መጠቀሚያ እንዲሁም ቀሪውን 50 በመቶ በእለታዊ የውጭ ምንዛሬ መሸጫ ተመን እየታሳበ ክፍያ እንደሚያገኙም ነው የተሻሻለው የወርቅ ግብይት መመሪያ የሚጠቁመው።
ከዚህ ቀደም ወርቅ የሚሸጡ ኩባንያዎች ከሽያጩ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሬ ይዘው መጠቀም የሚችሉት ለአንድ ወር እንደነበር በማውሳትም አዲሱ መመሪያ ግን ወደ ሶስት ወራት እንዳሳደገው ባንኩ ይፋ አድርጓል።