ማኑኤል ኡጋርቴ ለህክምና ምርመራ ዛሬ ወደ ማንችስተር ያቀናል
ፒኤስጂ እና ማንችስተር ዩናይትድ በመሀል ሜዳ ተጫዋቹ ዝውውር ዙርያ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል
ኡጋርቴ በዘንድሮው የዝውውር መስኮት የዩናይትድ የመጨረሻው ፈራሚ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው
ማኑኤል ኡጋርቴ ለህክምና ምርመራ ዛሬ ወደ ማንችስተር ያቀናል።
ማንችስተር ዩናይትድ እና የፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ በኡራጋዊው አማካይ ማኑኤል ኡጋርቴ ዝውውር ላይ መስማማታቸው ተነገረ፡፡
የ23 አመቱ አማካይ ኡጋርቴ የዝውውር መስኮቱ ከተከፈተ ጀምሮ ዩናይትድ በጥብቅ ከሚፈልጋቸው ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡
ረጅም ጊዜያትን በፈጀው የዝውውር ሂደት ዩናይትድ ተጫዋቹን ለማስፈረም ከፒኤስጂ ጋር የተለያዩ የድርድር ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ስካይ ስፖርት ዛሬ ይዞት በወጣው መረጃ ዩናይትድ ተጫዋቹን ለማስፈረም ለፈረንሳዩ ክለብ 51 ሚሊየን ፓውንድ ለመክፈል ተስማምቷል፡፡
ኡጋርቴ ፊርማውን ለማንችስተር ዩናይትድ ከማኖሩ በፊት በዛሬው እለት ወደ እንግሊዝ ተጉዞ የህክምና ምርመራውን የሚያከናውን ሲሆን በተጨማሪም በግል ጥቅማ ጥቅሞች ዙርያ ከክለቡ ሃላፊዎች ጋር እንደሚነጋገር ይጠበቃል፡፡
ከስፖርቲንግ ሊስበን በ51.1 ሚሊን ዩሮ ፒኤስጂን የተቀላቀለው ተጫዋቹ በክለቡ የቆየው አንድ አመት ብቻ ነው፡፡
የማሀል ሜዳ ክፍል ተጫዋቹ በፈረንሳዩ ክለብ በነበረው ቆይታ በብዛት የቋሚ ተሰላፊነት ስፍራን ባያገኝም ለክለቡ በተሰለፈባቸው 25 የሊግ ጨዋታዎች 98 ሸርታቴዎችን እንደወረደ ይነገራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ማንችስተር ዩናይትድ ስኮት ማክቶሚናይን ለጣሊያኑ ክለብ ናፖሊ ለመሸጥ ከስምነት ላይ መድረሱ ተሰምቷል፡፡
ክለቡ የመሀል ሜዳ ተጫዋቹን ስኮትላንዳዊ ማክቶሚናይን ለመሸጥ ከናፖሊ 30 ሚሊየን ዩሮ የሚቀበል ይሆናል፡፡
ካለፉት ሁለት እና ሶስት የውድድር ዘመናት የተሻለ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኝው ማንችስተር ዩናይትድ የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት የሚያስፈርመው የመጨረሻ ተጫዋች ማኑየል ኡጋርቴ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
በዘንድሮ የውድድር ዘመን መጀመርያ ጨዋታ ፉልሀምን አንድ ለዜሮ በሆነ ጠባብ ውጤት ያሸነፈው ዩናይትድ ባሳለፍነው ሳምንት ከብራይተን ጋር ባደረገው ጨዋታ 2ለ1 የተሸነፈ ሲሆን በመጪው ቅዳሜ ከተቀናቃኙ ሊቨርፑል ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል፡፡