የ39 አመቱ ሮናልዶ ጫማ ሲሰቅል በአሰልጣኝነት የመሰማራት እቅድ እንደሌለውም ገልጿል
ከ20 አመት በላይ በእግርኳስ ተጫዋችነት የዘለቀው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጭማ ሊሰቅል መቃረቡን የሚጠቁም አስተያየት ሰጥቷል።
ፖርቹጋላዊው ኮከብ “ናው” ከተሰኘው የሀገሩ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቆይታ፥ በቀጣዮቹ ሁለት ወይም ሶስት አመታት ውስጥ ጫማውን እንደሚሰቅል ተናግሯል።
በሪያል ማድሪድ ነግሶ፤ በማንቸስተር ዩናይትድ እና ጁቬንቱስ አንጸባርቆ ወደ በ2022 ወደ አል ናስር የዘለቀው ክርስትያኖ ሮናልዶ ለሳኡዲው ክለብ በ72 ጨዋታዎች 66 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።
የ39 አመቱ ኮከብ በአል ናስርም ሆነ በሳኡዲ እየመራው ባለው ህይወት ደስተኛ መሆኑን ገልጿል።
በርካቶች እንደሚያደርጉት የመጨረሻ የእግርኳስ ቆይታውን ወደ ልጅነት ክለቦ ስፖርቲንግ ሊዝበን ተመልሶ ጫማውን በዚያው ይሰቅላል ተብሎ ቢጠበቅም “ጫማዬን የምሰቅለው በዚሁ በአልናስር ክለብ ነው” ብሏል።
ፖርቹጋላዊው ኮከብ በአልናስርና በሀገሩ ፖርቹጋል ያላጠናቀቃቸው የቤት ስራዎች እንዳሉትም ነው ያነሳው።
ጀርመን ባዘጋጀችው የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ለሀገሩ ምንም ግብ ያላስቆጠረው ሮናልዶ፥ ክለቡ አልናስር ባደረጋቸው የሳኡዲ ፕሮ ሊግ ሶስት የመክፈቻ ጨዋታዎች ሶስት ጎሎችን አስቆጥሯል።
በየቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሪያል ማድሪድ እና ጁቬንቱስ አጥቂ በእግርኳስ ህይወቱ 898 ጎሎችን አስቆጥሯል። ከዚህ ውስጥ 130 ጎሎቹ ከፈረንጆቹ 2003 ጀምሮ ለሀገሩ ፖርቹጋል ያስቆጠራቸው ናቸው።
ሮናልዶ በአለማቀፍ ውድድሮች በመጫወት ለሀገሩ የተሻለ ነገር በማድረግ የእግርኳስ ህይወቱ ፍጻሜውን ቢያገኝ ፍላጎቱ መሆኑን ተናግሯል።
ፖርቹጋል ከቀጣዩ መስከረም ወር ጀምሮ ከክሮሺያ፣ ስኮትላንድ እና ፖላንድ ጋር የኔሽንስ ሊግ ጨዋታዎች አሉባት።
“ጫማ ከሰቀልኩ በኋላ አሰልጣኝ ለመሆን አንድም ቀን አስቤ አላውቅም” ያለው ሮናልዶ፥ በሻምፒዮንስ ሊግ ባጻፈው ደማቅ ታሪክ ከአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሴፈሪን ሽልማት ይቀበላል።
የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው በ183 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች 140 ጎሎችን በማስቆጠር የውድድሩ የምንጊዜም ግብ አስቆጣሪ ነው። ሊዮኔል ሜሲ በ129 ፤ የባርሴሎናው አጥቂ ሮበርት ሎዋንዶውስኪ ደግሞ በ94 የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ አምስት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ (አራት ከሪያል ማድሪድ እና አንድ ከማንቸስተር ዩናይትድ) ማንሳቱም የሚታወስ ነው።