በብልጽግና ፓርቲ የመተዳደሪያ ደንብ እና መሠረታዊ እሳቤዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው
በብልጽግና ፓርቲ የመተዳደሪያ ደንብ እና መሠረታዊ እሳቤዎች ላይ በአዲስ አበባ ውይይት እየተደረገ ነው
የአዲሱን የብልጽግና ፓርቲ የውህደት ሂደት ጨምሮ በቅርቡ በጸደቀው የመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ዛር ህዳር 26/2012 ዓ.ም. ውይይት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፡፡
የፓርቲውን ውህደቱን በተመለከተ በተደረጉ ጥናቶች ላይ ከአሁን ቀደም በየደረጃው ተከታታይ ውይይቶች መካሄዳቸውን የገለፁት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ውህደቱ ፖለቲካዊና ህጋዊ አግባቦችን ተከትሎ መፈፀሙን ገልፀዋል።
በስራ አስፈጻሚው የፀደቀው የመተዳደሪያ ደንብ የድርጅቱ መስራች ጉባዔ እስከሚካሄድ ድረስ ያገለግላል ያሉም ሲሆን በተለያዩ ሃሳቦች ሊዳብር እንደሚችልም ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በፕሮግራሙ የብሔር ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛንን የጠበቀ ማድረግ እንዲሁም አንድ ጠንካራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር አላማ እንዳለው ተነስቷል።
በተጨማሪም ኢሕአዴግ የነበሩት መልካም ተሞክሮዎችና ክፍተቶች ተነስተው በሚታረሙበት አግባብ ላይ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ከህወሓት ውጭ የኢህአዴግ እህትና አጋር ድርጅቶች ተሰባስበው የፈጠሩት ብልጽግና ፓርቲ ህጋዊ እውቅና ለማግኘት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡