ጎግል ለደቡብ አፍሪካ የዜና ማሰራጫዎች 500 ሚሊየን ራንድ ካሳ እንዲከፍል ተወሰነበት
ተቋሙ የዜና ማሰራጫዎቹን ይዘቶች በመጠቀም ከሚያገኘው ትርፍ የሚከፍለው ክፍያ ዝቅተኛ ነው ተብሏል

ጎግል የተጣለበትን የካሳ ክፍያ የማይከፍል ከሆነ የ10 በመቶ የታክስ ጭማሪ እንደሚደረግበት ተገልጿል
ደቡብ አፍሪካ ግዙፉ የመረጃ መፈለጊያ ተቋም ጎግል ለሀገሪቱ የዜና ማሰራጫ ተቋማት በየአመቱ 500 ሚሊየን ራንድ (27.29 ሚሊየን ዶላር) እንዲከፍል አዘዘች፡፡
የሀገሪቱ የውድድር ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ጎግል ፣ ሜታ እና ኤክስ (ትዊተር) የደቡብ አፍሪካ የዜና ማሰራጫ ተቋማትን ይዘቶች በመጠቀም ከሚያገኙት ትርፍ የሚከፍሉት ክፍያ ዝቅተኛ ነው ብሏል፡፡
ይህን ተከትሎም ጎግል ለአምስት አመታት በአመት 500 ሚሊየን ራንድ (የደቡብ አፍሪካ ገንዘብ) እንዲከፍል የተወሰነበት ሲሆን ሜታ እና ኤክስ ተመሳሳይ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የሜታ ኩባንያ በሚያስተዳድራቸው ፌስቡክ ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕን በመሳሰሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የደቡብ አፍሪካን የዜና ይዘት ሊንኮች (ማስፈንጠሪያዎች) ለብዙዎች ተደራሽ እንዳይሆን በመደበቅ ተከሷል፡፡
የውድድር ተቆጣጣሪ ኮሚሽኑ የጎግል አልጎሪዝም ባለፉት 14 አመታት በሀገር ውስጥ የዜና ማሰራጫ ጣቢያዎች መካከል ፍትሀዊ ውድድር እንዳይደረግ በቋንቋ እና በአለም አቀፋዊ ይዘቶች በመካፋፈል መድሎ ያደርግ እንደነበር በጥናት ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡
ይህም በጥቂት የዜና ማሰራጫዎች እና ቋንቋዎች መካከል ፍትሀዊ ያልሆነ የገበያ ውድድር ማስፈኑ ነው የተነገረው፡፡
ቅሬታውን ለማስተካከል ጎግል ለደቡብ አፍሪካ የዜና ማሰራጫዎች ከ300 እስከ 500 ሚሊዮን ራንድ በየአመቱ ከሶስት እስከ አምስት አመት ካሳ እንዲከፍል ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ከዚህ ባለፈም የዜና አፈላለግ እና ተደራሽነት ላይ በዜና ማሰራጫዎቹ መካከል ፍትሀዊ አሰራርን እንዲዘረጋ ጠይቋል፡፡
ተቆጣጣሪ ኮሚሽኑ ጎግልን ጨምሮ የፍትሀዊነት ጥያቄ የቀረበባቸው አካላት እስከ ሚያዚያ 7 ድረስ የቀረበባቸውን ክስ መሞገት የሚችል ማስረጃ እንዲያቀርቡም አዟል፡፡
ዩቲዩብን ጨምሮ ፌስቡክ ኤክስ እና ሌሎችም ማህበራዊ ትስስር ገጾ በቀረበባቸው ክስ እስከ 6 ወራት ድረስ በቂ ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ ከማስታወቂያ ገቢ በሚገኘው ታክስ ላይ የ10 በመቶ ጨማሪ እንደሚያደርግ አስጠንቅቋል፡፡
ሪፖርቱን በዝርዝር እየመረመረ እንደሚገኝ ያስታወቀው ጎግል በሰጠው ምላሽ በ2023 በጎግል ሰርች እና ጎግል ኒውስ 350 ሚሊየን ራንድ መሰብሰቡን፤ ከዚህ ውስጥ የተቋሙ ትርፍ 19 ሚሊየን ራንድ ብቻ መሆኑን ገልጾ እንዲከፍል የተጠየቀው የቅጣት ክፍያ የተጋነነ ነው ብሏል፡፡