ሩስያ ጎግል የምድር አጠቃላይ ገንዘብ ተሰብስቦ ሊሞላው የማይችለውን ገንዘብ እንዲቀጣ ወሰነች
ጎግል 17 የሩስያ መንግስት መገናኛ ብዙሀንን ከዩትዩብ ላይ ማገዱን ተከትሎ 20 ዴሲሊየን ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል
ሞስኮ የጠየቀችው ክፍያ ከትሪሊየን ቀጥሎ 7ተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የ34 ዜሮ ባለቤት ከፍተኛ ቁጥር ነው
የሩሲያ ፍርድ ቤት ጎግል ከዩቲዩብ ላይ የሩሲያ መንግስት የቴሌቪዝን ጣብያዎችን ማገዱን ተከትሎ 20 ዲሲሊየን ዶላር($20,000,000,000,000,000,000,000,000,000,000,000.) እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
ጎግል ምንም እንኳን ከአለማችን ትርፋማ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ቢሆንም የድርጅቱ አጠቃላይ ዋጋ ከ2 ትሪሊየን ዶላር የሚሻገር አይደለም፡፡
በዚህም የሩስያ ፍርድ ቤቶች የጣሉት ቅጣት 100 ተመሳሳይ ዋጋ ያላቸው ኩባንያዎች እንኳን ተደምረው ሊከፍሉት የሚችሉት አለመሆኑ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የተጠየቀው ገንዘብ ከአለም አቀፍ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (ጂዲፒ) እድገትም የሚበልጥ ነው፡፡
እንደ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) መረጃ ከሆነ በአሁኑ ወቅት የአለም አቀፍ ጥቅል ሀገራዊ ምርት እድገት 110 ትሪሊየን ዶላር ነው፡፡
ቅጣቱ በ2020 ጎግል በሩሲያ አገልግሎት መስጠት ማቆሙን ተከትሎ ተጥሎ የነበረ ሲሆን በየቀኑ በእጥፍ እየጨመረ አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
በጎግል እና በሩስያ መካከል ቅራኔ የተፈጠረው የዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ ሁለት አመት ቀደም ብሎ የነበረ ሲሆን በ2022 የዩክሬን ጦርነት ሲጀመር ሌሎች ምዕራባውያን ኩባንያዎች በሞስኮ ላይ ተጽዕኖ ለማሳረፍ ግንኙነታቸውን ማቋረጣቸውን ተከትሎጎግልም ተመሳሳዩን አድርጓል፡፡
በዚህም ታዋቂዎቹን የሩስያ መገናኛ ብዙሀን አርቲ እና ስፑትኒክን ጨምሮ 17 መገናኛ ብዙሀን በዩትዩብ ላይ እንዳይገለገሉ ገጻቸውን አግዷል፡፡
በተመሳሳይ የሩስያ ሚድያዎች በአውሮፓ መስራት እንዳይችሉ ተከልክለዋል። ሞስኮም በተመሳሳዩ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ከልክላለች፡፡
ይህ ሁኔታ በሞስኮ እና በግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ መካከል ያለውን ቅራኔ እንዲባባስ እንዳደረገው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ቁጥሩን በትክክል እንኳን መጥራት እንደማይችሉ በይፋ ያመኑት የክሪምሊን ቃልአቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የጎግል አስተዳደር ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
ጎግል በሩስያ ፍርድ ቤቶች እንዲከፍል በተጠየቀው በምድር ላይ በሌለ ገንዘብ ዙርያ እስካሁን በይፋ የሰጠው መግለጫም ይሁን ምላሽ የለም፡፡
ከትሪሊየን በኋላ ያሉ ቁጥሮች እምብዛም ጥቅም ላይ ሲውሉ አይታዩም፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንድ በአዋቂ እድሜ ላይ በሚገኝ የሰው ልጅ ሰውነት ውስጥ 7.1 ኦክታሊየን የአተም ቅንጣቶች እንደሚገኙ ሳይንስ ይናግራል፡፡