ጎግል ኢትዮጵያዊቷን የኮምፒዩተር ሳይንቲስት ከስራ ማሰናበቱ እያነጋገረ ነው
በተቋሙ ስለሚስተዋሉ የዘር እና የጾታ መድሎዎች ማጋለጧ ለትምኒት ከስራ መሰናበት ምክንያት ነው ተብሏል
በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቋሙ ሰራተኞች ማብራሪያ እንዲሰጣቸው በደብዳቤ ጠይቀዋል
ጎግል ኢትዮጵያዊቷን የኮምፒዩተር ሳይንቲስት ከስራ ማሰናበቱ እያነጋገረ ነው
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኮምፒዩተር ሳይንቲስት ትምኒት ገብሩ በከፍተኛ ተመራማሪነት ትሰራበት ከነበረው ዓለም አቀፉ የኦንላይን የመረጃ ማፈላለጊያ ተቋም ጉግል መሰናበቷ እያነጋገረ ነው፡፡
ትምኒት በጎግል የስነ ምግባራዊ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Ethical Artificial Intelligence) የስራ ክፍል ውስጥ በተባባሪ ቡድን መሪነት ነበር የምትሰራው፡፡
ተጠቃሚን በፊት ገጽ ለመለየት አግልግሎት ላይ በሚውሉ ቴክኖሎጂዎች የዘር አድሎ እና ሌሎችም ተያያዥ የምርምር ስራዎቿም ትታወቃለች፡፡
እነዚህን የመድሎ እና የአሰራር ክፍተቶች በማጋለጧም ነው ከስራ የተሰናበተችው፡፡
ይህንንም ከሰሞኑ በተከታታይ የማህበራዊ ገጽ ጽሆፎቿ አስታውቃለች፡፡
ተከታታይ ኢ-ሰብዓዊ የሆኑ ጫናዎች ይደረጉባት እንደነበርም ነው ትምኒት የገለጸችው፡፡
ዋሽንግተን ፖስት ለትምኒት ከስራ መሰናበት ለበታች ሰራተኞች የላከችው ትችት አዘል የኢሜይል መልዕክት የቅርብ ምክንያት እንደሆነ ዘግቧል፡፡
ኤን.ፒ.አር ደግሞ የትምኒት ከስራ መሰናበት በተቋሙ ሰራተኞች ዘንድ ቁጣን እንደቀሰቀሰ ነው ያሰፈረው፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች በጻፉት ደብዳቤ ደግሞ ግልጽ ማብራሪያን ከጉግል ጠይቀዋልም ብሏል፡፡
የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ምሩቋ ትምኒት በኤሌክትሪካል ምህንድስና እስከ ሶስተኛ ዲግሪ መዝለቋን የህይወት ታሪክ መረጃዎቿ ይጠቁማሉ፡፡