የኤርትራ ዜጎች ከኢትዮጵያ እንዳይወጡ አለመከልከሉን መንግስት አስታወቀ
ኢትዮጵያ 1 ሚልየን ገደማ ስደተኞች ተቀብላ በመስተናገድ ዓለም አቀፍ ኃላፊነቷ እየተወጣች ያለች ሀገር መሆኗ ይታወቃል
ህግን በሚጣረስ መልኩ ኢትዮጵያን ለቀው ለመውጣት የሚፈልጉ ኤርትራውያን መኖራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል
የኤርትራ ዜጎች ከኢትዮጵያ እንዳይወጡ መንግስት አለመከልከሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ ላይ “የኤርትራ ዜጎች ከኢትዮጵያ እንዳይጡ ይከለከላሉ” በሚል ለቀርበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህም አምባሳደር ዲና፤ መንግስት ከኢትዮጵያ እንዳይወጡ ተከልክለዋል ስለተባሉትና የኤርትራ ፓስፖርት የያዙ የውጭ ሀገር ቪዛ ያላቸውን ጉዳይ በጥንቃቄ ይመረምራል ሲሉ ተናግረዋል።
በኤርትራውያን በኩል የሚነሳ ቅሬታ ሚኒሰቴር መስሪያ ቤታቸው በተለያየ መልኩ እንደሚሰማ ያነሱት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ “ጉዳዩ በዋናነት ከህግ፣ ከሰነድ እንዲሁም ከደህንነት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ መንግስት ነገሮችን በተጠና መልክ ለመስራት እየጣረ ነው” ሲሉ ብለዋል።
የሀገሪቱ ህግ እና ሂደቶች በሚጣረስ መልኩ ኢትዮጵያን ለቆ ለመውጣትና የመቻኮል (እዚህ ሀገር ካልሄድን ወዘተረፈ የሚሉ) ሁኔታዎች ቢኖሩም፤ ሁሉም ነገር ግን በህጉ መሰረት ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናልም ብለዋል ቃል አቀበዩ።
የ1951ዱን የስደተኞች ኮንቬንሽንና የ1967ቱን ፕሮቶኮልም የፈረመችው ኢትዮጵያ ፣ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን /ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር/ እና ሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በመሆን ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቷን በመወጣት ላይ ናት።
ይሁንና ኢትዮጵያ ከምታስተናግዳቸው የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች አልታጡም።
በተለይም ኤርትራውያን ስደተኞች፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየሞች) አካባቢ በሚፈጥሩት የድምጽ ብክለት “ነዋሪዎች ቤታቸውን አከራይተው ከአካባቢው እንዲርቁ” ምክንያት ከመሆን ባለፈ፣ “ተደራጅተው የመዝረፍ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉም” ቅሬታ ሲቀርብባቸው ይስተዋላል።
ለዚህም በህጋዊ መንገድ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ኤርትራውያን እንዳሉ ሁሉ በተጭበረበረ መንገድ የመታወቂያ ወይንም ፓስፖርት አውጥተው የሚንቀሳቀሱ ኤርትራውያን መኖራቸው ጉዳዩ አሳሳቢ እንዳደረገው ይነገራል።
ኢትዮጵያ ከ 27 ሀገራት በተለይም ከሶማልያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ የመጡ ስደተኞችን እንደምታስተናግድ ይታወቃል።
የኢፌድሪ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አገልግሎት መረጃ እንደሚያመለክተው ፣ አሁን ላይ 324 ሺ የደቡብ ሱዳን ፣ 217ሺ የሚገመቱ የኤርትራ፣ 200ሺ የሶማልያ ፣ 67ሺ የሱዳን ፣ እንዲሁም 5ሺ የኬንያ ስደተኞች በኢትዮጵያ ይገኛሉ።
በአጠቃላይ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ 1 ሚልየን ገደማ የሚሆኑ ስደተኞችን በማስተናገድ፡ በአፍሪካ ከኡጋንዳና ሱዳን ቀጥላ ኢትዮጵያ በሶስተኛ ደረጃ ተቀምጣለች።