ግብጽ ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራውያንን እያባረረች ነው መባሉን ተመድ አወገዘ
ካሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት ወዲህ 70 ገደማ ኤርትራውያን ስደተኞች በሁኔታዎች ተገደው ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው ነው የተነገረው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የካይሮን ድርጊት ከዓለም አቀፍ ህግጋት የሚቃረን ነው ሲል አውግዟል
ግብጽ ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራውያን ስደተኞችን እያባረረች ነው መባሉ እያነጋገረ ነው፡፡
ካይሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከሃገራቸው ወጥተው ጥገኝነት የጠየቁትን ስደተኞች እያበረረች መሆኗ እያነጋገረም ይገኛል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድርጊቱ ግብጽን አውግዟል፡፡ ስደተኞችን ከተመለከቱ ዓለም አቀፍ ህግጋት የሚቃረን እንደሆነ በመጥቀስም ነው የድርጅቱ ባለሙያዎች የካይሮን እርምጃ ያወገዙት፡፡
ባለሙያዎቹ ግብጽ ጥገኝነት በሚጠይቁ ኤርትራውያን ላይ እየወሰደች ያለውን እርምጃ ሀገሪቱ ልትወጣው የሚገባ ዓለም አቀፍ ግዴታን ከግምት ያላስገባና የሚቃረን ነው ብለዋል፡፡
"ግብጽ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየወሰደች ያለውን ኤርትራውያንን በጅምላ የማባረር እርምጃ ልታቆም ይገባል" ሲሉ መጠየቃቸውንም የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም ወደ ሀገራቸው የተባረሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኤርትራ ከተመለሱ በኋላ ለስቃይና እንግልት መዳረጋቸውና የአንዳንዶቹ ደብዛ መጥፋቱንም ነው መግለጫው የሚያትተው፡፡
"በጅምላ የማባረር ድርጊት በዓለም አቀፍ ህግ ክልክል ነው" ሲልም አስቀምጧል፡፡
ኤርትራ በተመድ የሰብአዊ መብቶች ም/ቤት አባል ሆና በድጋሚ ተመረጠች
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግብጽ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ እየወሰደች ያለውን በጅምላ የማባረር እርምጃ እንድታቆም ባለፈው ወር መጠይቁ አይዘነጋም፡፡
አምነስቲ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ እንደሆነም በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት ግለጾ ነበር፡፡
በሪፖርቱ እንደተቀመጠው ማብራሪያ በተጠናቀቀው መጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት 31 ኤርትራውያን ወደ ሃገራቸው የተመለሱ ሲሆን ሌሎች ከሰባት አመት በታች ያሉ ሶስት ህጻናትን ጨምሮ 50 ሰዎች ተመሳሳይ እጣፈንታ ሲጠባበቁ ነበር፡፡
ከጥቅምት 2021 ወዲህ 68 ኤርትራውን ሳይፈልጉ በግድ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ መደረጉንም ነው አምነስቲ በሪፖርቱ የጠቀሰው፡፡
ከተመድ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት መሃመድ ዓብደልሰላም ባቢከር (ዶ/ር) "ሳይፈልጉ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ የተደረጉት ስደተኞች ወደ ኤርትራ ከተመለሱ በኋላ አብዛኞቹ ሰው በቀላሉ ሊያገኛቸው ወደማይችል እስር ቤት ይገባሉ፤ ደብዛቸው የጠፋም አሉ" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ግብጽ፤ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሃገሯ የሚገቡ ኤርትራውያን ስደተኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል፤ በርካቶቹን ወደ ሀገራቸው የምትመልስ ሲሆን አንዳንዶቹን ለዓመታት በእስር ቤት አጉራ በማቆየት ትታወቃለች፡፡
በኤርትራ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን የአፍሪካ ሀገራት ድንበር አሳብረው ወደ አውሮፓና ሌሎች ሀገራት ለመሰደድ መገደዳቸውን የተመድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የተመድ መርማሪዎች ሁኔታውን በተመለከተ ወደ ሃገሯ ገብተው አስፈላጊውን ምርመራ እንዳያደርጉ ከልክላለች በሚል ኤርትራ በተደጋጋሚ ትወቀሳለች፡፡
ሆኖም የኤርትራ ባለስልጣናት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ክስ የሃገሪቱን ገጽታ ለማጠልሸት በማሰብ የሚቀርብ ነው በሚልክሱን ደጋግመው ውድቅ አድርገዋል፡፡