ኤርትራ፤ ብሪታኒያ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመመለስ የያዘችውን እቅድ “አሳፋሪ” ስትል ነቀፈች
በርካታ ኤርትራውያን በፈረንሳይ በኩል ጀልባዎችን በመጠቀም ወደ ብሪታንያ እንደሚገቡ መረጃዎች ያሳያሉ
የኤርትራ መንግስት “ሩዋንዳ ለገንዘብ በማለት የእቅዱ አካል መሆኗ ልትወገዝ ይገባል” ብሏል
የኤርትራ መንግስት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የሚመለስውን የብሪታኒያ እቅድ “አሳፋሪና ርካሽ” ሲል ነቀፈ።
የብሪታኒያ መንግስት በሀገሩ የሚገኙ ስተደኞችን በአንድ ነጠላ ትኬት ወደ ሩዋንዳ እንደሚልክ ባሳለፍነው ሳምንት ማሰወቁ ይታወሳል።
ሩዋንዳም በብሪታኒያ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን ለመቀበል የሚልየን ዶላሮች ስምምነት ከቀናት በፊት ፈርማለች።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ይህንን ተከትሎ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ሩዋንዳ ለገንዘብ ስትል የእቅዱ አካል መሆኗ ልትወገዝ ይገባል ብሏል።
"ለገንዝብ ሲባል በብሪታኒያና እና አንዲት የአፍሪካ ሀገር ትብብር አማካኝነት የሚደረግ አሳፋሪ ድርጊት ሁሉም ሊያወግዘው የሚገባ ነው" ይላል የሚኒሰቴሩ መግለጫ።
በርካታ ኤርትራውያን፤ በፈረንሳይ በኩል ጀልባዎችን በመጠቀም ወደ ብሪታንያ እንደሚገቡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ብሪታንያ ያወጣችው ፖሊሲም ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡትን ወንድ ስደተኞችን ለመቆጣጠር ያለመ እንደሆነ ተነግሯል።
ፖሊሲው የነገሮችን መነሻዎችና ባህሪያቶችን ከግምት ያላስገባ ነው ያለው የኤርትራ መግለጫ፤ "አንዳንድ ሀገራት ለሌላ የፖለቲካ ዓላማ ሲሉ ሌሎች ሀገራት (አፍሪካ) በሌሎች ሀገራት ተቃራኒ እያሰለፉና ስትራቴጂካዊ የማዳከም ተግባር ላይ እያሰማሩ ለመሆናቸው ማሳያ ነው" ብሏል።
ኤርትራ እንዲህ ትበል እንጂ፤ የበርካታ ኤርትራውያን ሀገራቸውን ትተው የመሰደድ ምክንያት በሀገሪቱ ያለው አስገዳጅ የብሄራዊ አግልግሎትና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መሆኑ በርካታ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይገልጻሉ።
ሩዋንዳ ፤ በብሪታኒያ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን ለማስተናገድ የሚያስችል እስከ 157 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ ስምምነት ከቀናት በፊት መፈረሟ ይታወሳል።
ስምምነቱ፤ ስደተኞች ከሩዋንዳዉያን ጋር ተቀላቅለው ለመኖር የሚያስችል ነው ተብሎለታል።
የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪንሴንት ቢሩታ "ስምምነቱ የስደተኞችን ደህንነት እና ክብር የሚያስጠብቅ እንዲሁም የመኖር ፍላጎት ካላቸው በቋሚነት እንዲሰፍሩ መብት የሚሰጥ ነው" ማለታቸው አይዘነጋም።
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ መንግስታቸው ህገ-ወጥ ስደትን ለመግታት እንደሚሰራ በተለያዩ ጊዜያት ቃል ሲገቡ ይደመጣል። ይሁን እንጂ ህገ ወጥ ስደት በእሳቸው የስልጣን ዘመን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ይነገራል።
ብሪታኒያ፤ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለይም ከአፍሪካ የሚመጡ ስደተኞች በጥገኝነና በስደተነኝነት የሚኖርባት ሀገር መሆኗ ይታወቃል።