የቀድሞው የጣሊያን መሪ የቤንቶ ሞሶሎኒ የልጅ ልጅ የአውሮፓ ፓርላማ አባል ሆኑ
አሌሳንድራ ሞሶሎኒ የተሰኙት የልጅ ልጃቸው በጣልያን ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ናቸው
ቤንቶ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመውረር ጦር የላኩ መሪ መሆናቸው ይታወሳል
የቀድሞው የጣሊያን መሪ የቤንቶ ሞሶሎኒ ልጅ የአውሮፓ ፓርላማ አባል መሆናቸው ተገለፀ።
የጣልያን ፋሺስታዊ አስተዳድር መስራች ናቸው የሚባሉት የቤንቶ ሞሶሎኒ ልጅ ልጃቸው አሌሳንድራ ሞሶሎኒ ሀገራቸውን ወክለው የአውሮፓ ምክር ቤት አባል መሆናቸውን አርቲ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ አሌሳንድራ ከፈረንጆቹ 2014 እስከ 2019 ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ጣልያንን ወክለው የአውሮፓ ምክር ቤት አባል ሆነው አገልግለዋል።
ይሁንና በ2020 በተደረገው ምርጫ ዳግም ሳይመረጡ የቀሩት አሌሳንድራ ከፖለቲካ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተናግረው ነበር።
ከዚህ በፊት የፎርዛ ኢጣሊያ ፓርቲ አባል የነበሩት አሌሳንድራ ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ በተደረገው የጣልያን ምክር ቤት ምርጫ የጣልያን ማህበራዊ ንቅናቄ ፓርቲን ወክለው ዳግም ወደ ፖለቲካ መመለሳቸው ተገልጿል።
አሁን ላይ ጣልያን በአውሮፓ ፓርላማ ምክር ቤት ውስጥ ስምንት ተወካዮች ያሉ ሲሆን፤ አሌሳንድራ ሞሶሎኒ እነዚህም የምክር ቤት አባላት ከሚተኩት ውስጥ አንዷ ሆነው የአውሮፓ ፓርላማ አባል ይሆናሉም ተብሏል።
የሶስት ልጆች እናት የሆኑት እና በፈረንጆቹ 1962 በሮም የተወለዱት አሌሳንድራየትወና እና ሞዴሊንግ ሙያ የሰሩ ሲሆን ሮማኖ የተሰኘው ልጃቸው ለጣልያኑ ላዚዮ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ለመጫወት መፈረሙ ተገልጿል።
አሌሳንድራ የፈሺዝም አስተሳሰብ መስራች ለሆኑት እና ጣልያንን ከፈረንጆቹ 1922 እስከ 1943 ባሉት ዓመታት ውስጥ ለመሩት አያታቸው ቤኒቶ ሞሶሎኒ ስማቸው በመጥፎ ሲነሳ ይከላከሉ ነበርም ተብሏል።
ቤኒቶ ሞሶሎኒ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን የሚመራው ህብረት መሸነፉን ተከትሎ ነበር በፈረንጆቹ 1945 ስርዓቱን በተቃወሙ ጣልያናዊያን የተገደሉት።
ከሁለት ወር በፊት በተካሄደው የጣልያን ምክር ቤት ምርጫ የሀገሪቱ ቀኝ አቅራሪ ፓርቲዎች ዳግም ወደ ስልጣን የተመለሱ ሲሆን የጣልያን ማህበራዊ ንቅናቄ ፓርቲ መሪ የሖኑት ጆርጂያ ሜሎኒ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።
ይህም ጣልያን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን ተመልሰዋል ተብሏል።