ግሪክ ሲፈታተናት የከረመውን ሰደድ እሳት ተቆጣጠረች
በአደጋው የግሪክ ጥንታዊ የኦሎምፒክ ስፍራዎች ጭምር አደጋ ላይ ወድቀው እንደነበር መነገሩ የሚታወስ ነው
ሰደድ እሳቱ ከ100 ሺ ሄክታር በላይ መሬት ማዳረሱ ተነግሯል
ለባለፉት 2 ሳምንታት ግሪክን ሲፈትን የሰነበተው ሰደድ እሳት በቁጥጥር ስር መዋሉን የሃገሪቱ የዜጎች ጥበቃ የድንገተኛ እና እሳት አደጋዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ጽህፈት ቤቱ ከትናንት ሃሙስ ጀምሮ በአንዳንድ ኪስ ቦታዎች ካልሆነ በስተቀር ለቁጥጥር ያስቸገረ እሳት እንዳላጋጠመ አስታውቋል፡፡
ላለፉት 10 ቀናት ግሪክ ሲፈታተን የከረመው ሰደድ እሳት ከፍተኛ ስነ ምህዳራዊ ጉዳትን አስከትሏል፡፡
ሆኖም አሁን እሳቱ አስቸግሮ በነበረባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ መጣሉንና የሙቀት መጠኑ መቀነሱን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
ክፉኛ በጎዳቸው ኢቪያን መሰል አካባቢዎች ዳግም ሊቀሰቀስ የሚችልበት ሁኔታ እንዳይኖር በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝም ነው ጽህፈት ቤቱ ያስታወቀው፡፡
በቀጣዮቹ ቀናት ጠንከር ያለ ንፋስ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ማመልከታቸውን ተከትሎ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝም ነው የጽህፈት ቤቱ ቃል አቀባይ የተናገሩት፡፡
በሜዲትራንያን ባህር አካባ ሃገራት ያጋጠመውን ከፍተኛ የሙቀት መጠን ተከትሎ የተቀሰቀሰው የእሳት ሰደድ ከባድ ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡
ሰደድ እሳቱ ከ100 ሺ ሄክታር በላይ መሬት ማካለሉንም ነው የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች የዘገቡት፡፡
ግማሽ ያህሉ ጉዳት በኢቪያ ደሴት አካባቢ የደረሰ ነው፡፡
በሰደድ እሳቱ የግሪክ ጥንታዊ የኦሎምፒክ ስፍራዎች ጭምር አደጋ ላይ ወድቀው እንደነበር መነገሩም የሚታወስ ነው፡፡
አደጋውን ለመቋቋም የሚያስችሉ የመልሶ ግንባታ ስራዎች በቶሎ መሰራት እንደሚጀምሩም የሃገሪቱ ጠ/ሚ ኪርያቆስ ሚጾታኪስ ተናግረዋል፡፡
ጠ/ሚ ኪርያቆስ ከ15 ቀን በኋላ ለሃገሪቱ ፓርላማ አደጋውንየተመለከተ ማብራሪያ እንደሚሰጡም ተነግሯል፡፡
የተለያዩ 25 ሃገራት አደጋውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ድጋፎችን ለግሪክ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡