የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ ከግድያ መትረፋቸውን አስታውቀዋል
በጊኒ ቢሳው የተደረገ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መክሸፉ ተገለጸ፡፡
የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጊኒ ቢሳው ወታደሮች በፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ የሚመራውን መንግስት በመፈንቅለ መንግስት ለማስወገድ ሙከራች ተደርገዋል፡፡ ከትናንት ምሽት ጀምሮ 5፡00 የፈጀ የተኩስ ልውውጥ ነበረ፡፡
የተኩስ ልውውጡን ተከትሎ የነበረው የመፈንቅለ መንግስቱ ሙከራ መክሸፉ የተገለጸ ሲሆን ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ ከተቃጣባቸው ግድያ መትረፋቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
መፈንቅለ መንግስት በተደጋጋሚ በሚጎበኛት ጊኒ ቢሳው አሁን ላይ ሙስና እና አደገኛ ዕጽ ዝውውር የፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ ዋነኛ ፈተና ሆኖባቸዋል ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን እንዳሉት “ፈጣሪ ይመስገን፣ እኔ ደህና ነኝ አሁን ሁሉም ነገር በቁጥጥር ስር ውሏል” ብለዋል፡፡
ይሁንና አሁንም በአገሪቱ ዋና ከተማ ቢሳው የተኩስ ድምጾች በመሰማት ላይ ሲሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችም ወደ ሌላ ቦታዎች በመሸሽ ላይ መሆናቸውን ዘገባው አክሏል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ ወታደሮች በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን መቆጣጠር የተለመደ ሲሆን ጊኒ ቢሳው ነጻነቷን ከቅኝ ገዢዎች ከተጎናጸፈችበት ከፈረንጆቹ 1974 ወዲህ አራት ጊዜ መፈንቅለ መንግስት አስተናግዳለች፡፡
በአካባቢው አገራት እየተበራከተ የመጣው የመፈንቅለ መንግስት ያሳሰበው የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢኮዋስ በነገው ዕለት በዚሁ ጉዳይ በጋና መዲና አክራ ለመምከር ቀጠሮ ይዟል፡፡
የ49 ዓመቱ የጊዚ ቢሳው ፕሬዘዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደውን ምርጫ አሸንፈው አሸንፈው አገሪቱን በመምራት ላይ ናቸው፡፡