የቡርኪና ፋሶ ጁንታ አግዶት የነበረውን ሕገ መንግስት ወደነበረበት መለሰ
የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ሌ/ኮ ፖል ዳሚባ የሽግግር ጊዜ ፕሬዝዳንት እንደሆኑም ይፋ አድርጓል
ውሳኔው መፈንቅለ መንግስት ከተፈጸመበት ከጥር 24 ወዲህ የተወሰደ ከፍተኛ እርምጃ ነው ተብሏል
መፈንቅለ መንግስት አድራጊው የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ ጁንታ አግዶት የነበረውን የሃገሪቱን ሕገ መንግስት ወደነበረበት መለሰ፡፡
ወታደራዊ ጁንታው ይህን ያደረገው የአፍሪካ ህብረት ቡርኪና ፋሶን በማናቸውም የህብረቱ ጉዳዮች ላይ እንዳትሳተፍ ማገዱን ተከትሎ ነው::
ህብረቱ እገዳው በሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እስኪከበር የሚጸና እንደሚሆን መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ከአፍሪካ ህብረት ባሻገር የምዕራብ አፍሪካ ዲፕሎማቶች እና የተባበሩት መንግስታት የቡርኪና ፋሶ አስተዳደር ወደ ሲቪል አገዛዝ እንዲመለስ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል፡
ይሁን እንጅ ጁንታው ስልጣን ከያዘበት ከአንድ ሳምንት በኋላ ህገ መንግስቱን መመለሱንና የመፈንቅለ መንግስቱን መሪ የሽግግር ጊዜ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መሾሙን እየገለጸ ነው፡፡
ጁንታው በሀገሪቱ ቴሌቭዥን በሰጠው መግለጫ “የሕገ መንግሥቱን እገዳ የሚያነሳ” መሰረታዊ ውሳኔ ማጽደቁንም አስታውቋል።
እንደ ኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ ከሆነ ውሳኔው መፈንቅለ መንግስት ከተፈጸመበት ከጥር 24 ወዲህ የተወሰደ ከፍተኛ እርምጃ ነው፡፡
በጁንታው የቀረበው የባለ 37 አንቀጽ ሰነድ መግለጫ ፤ ለዳኝነት ነፃነትን እና ንፁህ ነኝ ብሎ ማሰብን እንዲሁም በሕገ መንግስቱ ውስጥ የተቀመጡ መሰረታዊ ነፃነቶች ማለትም እንደ የመንቀሳቀስ እና የመናገር ነፃነት ዋስትናዎችን የሰጠ መሆኑም ተጠቅሷል።
ጁንታው ለራሱ ‘ፓትሪዮቲክ ሙቭመንት ፎር ሴፍጋርድ ኤንድ ሪስቶሬሽን’ (PMSR) የሚል ስያሜ የሰጠ መሆኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን “የሲቪል አስተዳደር የሽግግር አካላት እስኪቋቋሙ ድረስ የግዛቱን ቀጣይነት ያረጋግጣል” የሚል አንቀጽም በሰነዱ ማካተቱ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
መግለጫው ለሽግግሩ ጊዜ የጊዜ ገደብ አላስቀመጠም ነው የተባለው፡፡
የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ሌ/ ኮ ፖል ሄንሪ ሳንዳኦጎ ዳሚባ የPMSR ፕሬዝዳንት እንደሆኑም ይፋ አድርጓል።
ይህ ሚና የቡርኪናፋሶን ፕሬዝዳንት፤ የሀገር መሪ እና የጦር ሃይሎች ከፍተኛ መሪን ያጠቃልላል ሲልም መግለጫው አክሏል።
መግለጫው ንቅናቄው ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዳሉት ቢያመላክትም ምክትሎቹ ማን ናቸው ለሚለውም ምንም ስም አልጠቀሰም።