አምባሳደሩ በ72 ሰዓታት ውስጥ ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል
ማሊ ባማኮ የሚገኙት የፈረንሳይ አምባሳደር በ72 ሰዓታት ውስጥ ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች፡፡
አምባሳደሩ የፈረንሳይ ባለስልጣናት ያልተገባ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው ባማኮን በ3 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት፡፡
በኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የሚመራው የማሊ ወታደራዊ የሽግግር መንግስት ከሰሞኑ ከፈረንሳይ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጡን አስታውቆ ነበር፡፡
ውሳኔውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ፈረንሳይኛን ከብሔራዊ ቋንቋነት መሰረዙንና ባምባራ ኦፊሴላዊ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በሃገሪቱ የሚገኘው የፈረንሳይ ጦር በ72 ሰዓታት ውስጥ ማሊን ለቆ እንዲወጣ ሲልም አሳስቦ ነበር በመግለጫው፡፡
ማሳሰቢያው የፈረንሳይ ኤምባሲን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት በ72 ሰዓታት እንዲዘጉ የሚያዝም ነው፡፡
“የማሊ መንግስት በህዝቡ ጥያቄ መሰረት ከፈረንሳይ መንግስት ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ፣ ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት ማቋረጡን በይፋ ያስታውቃል”
“የማሊ መንግስት ከፈረንሳይ ጋር ያደረጋቸውን የትብብር ስምምነቶች ከጥር 24/2022 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ማቋረጡንም ያስታውቃል” ሲልም ነው ከወታደራዊ የሽግግር መንግስቱ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መግለጫ የሚነበበው፡፡
የኮሎኔል አሲሚ ጎይታ መንግስት በምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) የሚኖረውን ተሳትፎ ማቆሙንና ማሊም በይፋ ከቀጣናዊው ተቋም አባልነት ራሷን ማግለሏን አስታውቋል፡፡
መግለጫው ማሊያውያን የራሳቸውን እጣ ፋንታ በራሳቸው እንዲወስኑም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ይህን ተከትሎ የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዢን-የቨስ ለ ድሬይን የማሊ ወታደራዊ ጁንታ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
ጁንታው ቅቡልነት እንደሌለውም ነበር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ የነበረው፡፡
የፈረንሳይ መከላከያም ሁኔታዎች የማይፈቅዱ ከሆነ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል በማሊ ያሰማራውን ጦር እንደሚያስወጣ አሳውቋል፡፡
የፈረንሳይ ባለስልጣናትን ንግግር የኮነነው የኮሎኔል አሲሚ ጎይታ መንግስትም ባማኮ የሚገኙትን የፈረንሳይን አምባሳደር ለማብራሪያ ጠርቶ ነበር፡፡
ከውይይቱ በኋላም አምባሳደሩ ባማኮን በ72 ሰዓታት ለቀው እንዲወጡ አዟል፡፡ እርምጃውን በተመለከተ ፈረንሳይ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የሰጠችው ይፋዊ ምላሽ የለም፡፡