የጊኒ አቃቤ ህግ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ኮንዴ ላይ ክስ እንዲመሰረት አዘዘ
የአቃቤ ህግ ሰነዶች እንደሚጠቁሙት፤ ኮንዴና እና ደጋፊዎቻቸው በግድያ፣ በጠለፋ፣ በማሰቃየት እና በህገወጥ እስራት ተከሷል
አዲሱ ክስ፤ ከሳምንታት በፊት ከእስር የተፈቱት ኮንዴን የቁም እስረኛ ሊያደርጋቸው ይችላል ተብሏል
የጊኒ አቃቤ ህግ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ እና 26 ባለስልጣኖቻቸውን አወዛጋቢ በሆነ መልኩ ለሶስተኛ ጊዜ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር በሚል ለፈጠሩት ረብሻ ክስ እንደሚመሰርት አዘዘ።
የ84 አመቱ የቀድሞ መሪ ፤አሁን ሀገሪቱን እያስተዳደረ ባለና በኮሎኔል ማማዲ ዱምቡያ የሚመራው ወታደራዊ ጁንታ አማካኝነት ፤በመስከረም ወር በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን መወገዳቸው የሚታወስ ነው፡፡
በጠቅላይ አቃቤ ህግ ቻርልስ አልፎንሴ ራይት የተፈረሙ ሰነዶች እንደሚጠቁሙት፤ የቀድሞው ፕሬዚዳንቱ እና ደጋፊዎቻቸው በግድያ፣ በጠለፋ፣ በማሰቃየት እና በህገወጥ እስራት ተባባሪ ሆነዋል የሚሉ የተለያዩ ክሶች ቀርበውላቸዋል፡፡
በዚህም የዲስትሪክቱ አቃቤ ህግ፤ በኮንዴ ላይ ህጋዊ ሂደቶችን በአስቸኳይ እንዲጀምር አዝዟል።
እንደፈረንጆቹ በ2020 በጊኒ የተቀሰቀሰው ብጥብጥ በዋና ከተማው በትንሹ 12 ሰዎች እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች 50 ሰዎች የሞቱበት እንደነበር ሰነዱ አመልክቷል።
ኮንዴ፤ ህገ-መንግስትን በማሻሻል የስልጣን ዘመናቸውን ለሶስተኛ ጊዜ ለማራዘም መሞከራቸው በሀገሪቱ ህዝቦች ዘንዳ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰና ለተፈጠረው ነውጥ ምክንያት የሆነ አጋጣሚ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ምንም እንኳን ገዥው ጁንታ ከሳምንታት በፊት ኮንዴ በሀገር ውስጥ መንቀሳቀስ እንደሚችሉና ወዳጆቻቸው ሊጠይቋቸው እንደሚችሉ ቢገለጽም፤ አዲሱ ክስ ምናልባት የቁም እስረኛ ሊያደርጋቸው ይችላል ተብሏል፡፡
ኮንዴ፤ መኖሪያ ቤታቸው እስኪታደስ በሚል በአሁኑ ጊዜ በኮናክሪ የሚስታቸው መኖሪያ ውስጥ እየኖሩ እንደሚገኙም ወታደራዊ ጁንታው በቅርቡ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በኮንዴ ላይ ህጋዊ ክስ እንዲመሰረት የተላለፈው ትዕዛዝ፤ የወታደራዊ ጁንታ መሪ ኮሎኔል ማማዲ ዱምቡያ ወደ ምርጫ ለማሸጋገር እና ወደ ሲቪል ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ለመመለስ ከሶስት አመታት በላይ ሊፈጅ እንደሚችል ከተናገሩ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ መሆኑ ነው።