ጊኒቢሳው እስካሁን ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ ሶስተ ሶወችን አስራለች
የቀድሞው የጊኒ ቢሳው ባህር አዛዥ በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ተጠርጥረው ታሰሩ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ጊኒቢሳው መፈንቅለ መንግስት ተሞክሮ መክሸፉ ይታወሳል፡፡
የ49 ዓመቱ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ በቢሯቸው ሚኒስትሮችን ሰብስበው እየተወያዩ ባሉበት ወቅት የታጠቁ ወታደሮች ወደ ቢሮ አቅንተው ተኩስ ከፍተውባቸው ነበር፡፡
ፕሬዘዳንቱን በመግደል ስልጣን በመፈንቅለ መንግስት መቆጣጠር ዋነኛው ዓላመው የነበረው ይህ ክስተት በቁጥጥር ስር ውሎ መፈንቅለ መንግስት ሙከራውም እንደከሸፈ ፕሬዘዳንቱ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር፡፡
በከሸፈው የጊኒቢሳው መፈንቅለ መንግስት 11 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በጉዳዩ ዙሪያ የተሳተፉ አካላትን የማደኑ ስራ መቀጠሉን ኤአፍፒ ዘግቧል፡፡
የሀገሪቱ አቃቢ ህግ ጉዳዩን በማጣራት ላይ ሲሆን እስካሁን በመፈንቅለ መንግስቱ ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በመያዝ ላይ ናቸው፡፡
የሀገሪቱ የቀድሞው ባህር ሀይል አዛዥ የነበሩት ጆሴ አሜሪኮ ቡቦ በዚህ መፈንቅለ መንግስት ላይ እጃቸው እንዳለበት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስራ መዋላቸውም ተገልጿል፡፡
ግለሰቡ በአደገኛ እጽ ዝውውር ላይ ተሳታፊ ነበሩ የተባለ ሲሆን ዝውውሩን ለማስቆም እየሰራ ባለው የፕሬዘዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎን መንግስት በሀይል ለማስወገድ አሲረዋል ተብሏል፡፡
ጊኒቢሳው ከላቲን አሜሪካ ወደ አፍሪካ በሚከናወነው አደገኛ ዕጽ ዝውውር ዋነኛ መስመር እንደሆነች የሚጠቀስ ሲሆን ዝውውሩ ውስብስብ እና አመራሮች ሳይቀር እንደሚሳተፉበት ይነገራል፡፡
የከሸፈው መፈንቅለ መንግስት የተቀነባበረው በቀድሞ የሀገሪቱ ወታደራዊ አመራሮች እና በአደገኛ እጽ ዝውውሩ ውስጥባሉ ዓለምአቀፍ ወንጀለኞች ጭምር እንደተሳተፉበት የጊኒቢሳው ፕሬዘዳንት ተናግረዋል፡፡