በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተወገዱት የጊኒ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ከእስር ተፈቱ
ኮንዴ አሁን ላይ ከሰዎች ጋር የመገናኘት ሙሉ ፈቃድ አግኝተዋል
በኮሎኔል ማማዲ ዱምቡያ የሚመራው ጦር ኮንዴን ከስልጣን ማስወገዱ ይታወሳል
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተወገዱት የጊኒ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ከእስር ተፈቱ ።
በጊኒ ወታደራዊው ጁንታ የተቋቋመው የብሔራዊ ኮሚቴ፤ የኮንዴ የግል መኖሪያ ቤት እድሳት እስኪደረግለት በባለቤታቸው መኖሪያ ቤት እንደሚቆዩ አስታውቋል።
ሰዎች ኮንዴ ወዳረፉበት ስፍራ በመምጣት ሊጎበኙዋቸው ይችላሉም ብሏል ኮሚቴው።
ኮንዴ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በቁም እስር የቆዩ ሲሆን፤ ባለፈው ጥር ወር ወደ አረብ ኢምሬትስ ሄደው በአቡ ዳቢ ህክምና ማግኘታቸውንም ተጠቅሷል።
የ83 አመቱ ኮንዴ እንደፈረንጆቹ በ2010 በጊኒ የመጀመሪያው በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ሲሆን፤ በ2015 በድጋሚ መመረጣቸው ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ፤እንደፈረንጆቹ በ2020 ስልጣናቸውን ለማራዘም ህገ-መንግስታዊ ለውጦች አድረገው ምርጫውን እንዳሸነፉ ማወጃቸው ከሀገሪቱ ወታደር ቤት አንስቶ አስከ ተራ ዜጎች አልተወደደላቸውም ነበር።
በዚህም በኮሎኔል ማማዲ ዱምቡያ የሚመራው ጦር ኮንዴን ባለፈው የፈረንቹ ዓመት መስከረም 5/2021 በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ማስወገዱ የሚታወስ ነው።
አልፋ ኮንዴ ከስልጣን መወገዳቸው ተከትሎ የጊኒ ወታደራዊ ጁንታ የቀድሞ የመንግስት ሰራተኛ የነበሩትን መሃመድ ቤቮጊን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም የወታደራዊ ጁንታ መሪ ኮሎኔል ማማዲ ዱምቦያ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አድርጎ እንደሾመም አይዘነጋም።