የጊኒ ጁንታ በጫና ፕሬዘዳንት አልፋ ኮንዴን ከእስር እንደማይለቅ ገለጸ
በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቆጣጠረው ጁንታ ፕሬዘዳንቱን እንዲለቅ ጫና እየተደረገበት ነው
በስልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዘዳንት አልፋ ኮንዴ ወደ እስር ቤት ከገቡ 15 ቀን ሆኗቸዋል
የጊኒ ጁንታ በጫና ምክንያት የቀድሞውን ፕሬዘዳንት አልፋ ኮንዴን ከእስር እንደማይለቅ ገለጸ።
የጊኒ ልዩ ሀይል አዛዥ የነበረው ማማዱ ዶምቢያ ከሁለት ሳምንት በፊት በስልጣን ላይ የነበሩትን ፕሬዘዳንት አልፋ ኮንዴ መፈንቅለ መንግስት በመፈጸም ወደ እስር ቤት መወሰዳቸው ይታወሳል።
- ኢኮዋስ ከመፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ በጊኒ እና በማሊ ጁንታዎች ላይ ማዕቀብ ጣለ
- የጊኒ መፈንቅለ መንግስት መሪ ኮሎኔል ማማዲ ደንቦያ የፈረንሳይ ጦር አባል ነበር ተባለ
ጉዳዩ የበርካቶችን ትኩረት የሳበ ሲሆን የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢኮዋስ እና የአፍሪካ ሀብረት በጊኒ ላይ ማዕቀብ ጥለዋል። ከዚያ ባለፈም የተለያዩ አገራት ጁንታው ስልጣኑን ለፕሬዘዳንት አልፋ ኮንዴ እንዲያስረክብ በመወትወት ላይ ሲሆኑ የጋና ፕሬዘዳንት ናና አኩፎ አዳ እና የኮቲዲቯሩ ፕሬዘዳንት አላሳና ኦታራ ወደ ጊኒ በማምራት ጎብኝተው ተመልሰዋል።
ፕሬዘዳንቶቹ ጁንታው ፕሬዘዳንቱን ከእስር እንዲለቃቸው እና አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እንዲያመቻችም ለማግባባት ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱን ሮይተርስ ዘግቧል። የጁንታው መሪ ማማዱ ዶምቢያ በእስር ላይ ያሉትን የቀድሞ ፕሬዘዳንት አልፋ ኮንዴ ከእስር እንደማይለቀቁ እና ማንኛውንም ጫና እንደማይቀበሉ በድጋሜ ይፋ አድርጓል።
በአፍሪካ ስልጣን በመፈንቅለ መንግስት መቆጣጠር የተለመደ ቢሆንም በምዕራብ አፍሪካ ግን በመደጋገም ላይ ይገኛል። በቅርቡም በማሊ በአንድ ዓመት ውስጥ በኮለኔል አስሚ ጎይታ መሪነት ሁለት ጊዜ መፈንቅለ መንግስት መፈጸሙ አይዘነጋም።