በመተከል አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር መንግሥት የበለጠ እንዲሰራ ኢሰመኮ አሳስቧል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ግልገል በለስ ከተማ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. የተፈጸመውን ጥቃት እና ከክስተቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ የአካባቢውን ነዋሪዎች፣ የክልሉን የጸጥታ እና የአስተዳደር ኃላፊዎች በማነጋገር ክትትል ማድረጉን ገልጿል።
እንደ ኢሰመኮ ሪፖርት ከሆነ ጥቃቱ የተፈጸመው በግልገል በለስ ከተማ፣ በተለምዶ “ቻይና ካምፕ” ተብሎ በሚጠራ ሰፈር ከቀኑ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ ነው።
በጥቃቱ ሶስት የአካባቢውን ሚሊሻ አባላት ጨምሮ 8 ነዋሪዎች መገደላቸውን፣ በ16 ሲቪል ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ የሕክምና እርዳታ እያገኙ መሆኑን፣ በርካታ ሌሎች ነዋሪዎች ቻይና ካምፕን ለቀው ወደ ሌላ ሰፈር መሸሻቸውንም ኢሰመኮ አስታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችና የአካባቢው አስተዳደር ኃላፊዎች የጥቃቱ ፈጻሚዎች በግልገል በለስ ከተማ አቅራቢያ ከመንግሥት ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ትጥቅ ለማስፈታት በሚል አንድ ካምፕ ውስጥ እንዲሰፍሩ የተደረጉ የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባላት እንደሆኑ ተገልጿል።
ታጣቂዎቹም ለጥቃቱ ምክንያት ያሉት “ከመንግሥት ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት አልተተገበረም” የሚል መሆኑን ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጫለሁም ብላል።
በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰባት አባላት ያሉትና በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያቀርብ የተቋቋመ ኮሚቴ፣ በመተከል ዞን ያለውን ሁኔታ ጎብኝቶ፣ ከሦስት ሺህ በላይ ታጣቂዎች እና በእነርሱ አማካኝነት “ጫካ ገብተው” የነበሩ ከ68 ሺህ በላይ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን መግለጹ የሚታወስ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ታጣቂዎቹ ትጥቃቸውን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር በተስማሙት መሠረት፣ በከተማዋ ምሥራቅ በኩል በሚገኝ ካምፕ እንዲሰፍሩ የተደረገ መሆኑን እና በተለምዶ “የሰላም ተመላሾች” በመባል እንደሚጠሩ ለማወቅ ተችሏል።
ሆኖም የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት፣ የታጣቂ ቡድኑ አባላት በከተማዋ ከነመሣሪያቸው ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ፣ በከተማዋ የሚገኙ የምግብ ቤት እና ሌሎች አገልግሎቶችን ሳይከፍሉ ወይም አገልግሎት ሰጪዎችን በማስገደድ በነጻ የሚጠቀሙ እና ከነዋሪዎች በግዳጅ ገንዘብ የሚሰበስቡ የቡድኑ አባላት እንዳሉ ኢሰመኮ በሪፖርቱ ገልጿል።
የቡድኑ አባላት በነዋሪዎች ላይ ወከባ፣ ማስፈራራት፣ ብሎም ድብደባ እና ሰዎችን በካምፕ አስሮ የማቆየት ተግባራትን የፈጸሙበት ጊዜ እንዳለ መሩዳቱን አስታውቋል።
መንግሥት በትቃቱ ምክንያት አካባቢውን ለቀው ወደ ሌላ ሰፈር ለሸሹ ነዋሪዎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ ማድረስ፣ ለነዋሪዎች አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ እንዲችሉ ማድረግ፣ እንዲሁም አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ በማድረግ ፍትሕን እንዲያረጋግጥ ኢሰመኮ አሳስቧል።