በአማራ ክልል መከላከያ ሰራዊትና ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
በግጭቱ ምክንያት ከአዲስ አበባ ደሴ ያለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተቋርጧል ተብሏል
የክልል ልዩ ሀይል መልሶ ማደራጀት በሚመለከት የተቃውሞ ሰልፍን አስተባብረዋል የተባሉ ወጣቶች እየታሰሩ መሆኑንም ኢሰመኮ ገልጿል
በአማራ ክልል የሀገር መከላከያ እና በአካባቢው ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ኢሰመኮ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ”ን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
ኮሚሽኑ ይህ ድርጊት በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለውን አንድምታና ተጽእኖ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ አደረኩት ባለው ክትትል በሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት አለ ብሏል።
- ግብረ ኃይሉ “በአማራ ክልል ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር በሚጥሩ ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደኩ ነው” አለ
- የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ሀላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ መገደላቸው ተገለጸ
በተለይም ሸዋ ሮቢት፣ አርማኒያ፣ አንጾኪያ፣ ገምዛ እና ማጀቴ በመከላከያ ሰራዊት እና በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥና በከባድ መሣሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት መኖሩን ደርሼበታለሁም ብሏል።
በዚህ የተኩስ ልውውጥ ምክንያትም በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ከመድረሱ ባለፈ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በተለያዩ ጊዜያት መዘጋቱን እንዳረጋገጠ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የተወሰኑ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማዋቀር ውሳኔን በመቃወም የተካሄዱ ሰልፎችን መርተዋል የተባሉ የተወሰኑ ወጣቶች እና ከፋኖ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች እንደታሰሩ ኢሰመኮ መረዳቱንም አስታውቋል።
በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ ተጨማሪ ግጭቶች ሰብአዊ መብቶች ላይ አስከፊ ወይም ከባድ ጥሰቶች የሚያስከትሉ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች ችግሩን በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱ አሳስቧል።
ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲቆጠቡ፣ ስለደረሰው ጉዳት ሁሉ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም ኢሰመኮ ጥቋል።
እንዲሁም በማናቸውም ሁኔታ የሚፈጸሙ እስራቶች ሕግን መሠረት ያደረጉ በተለይም “የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነጻ መሆን” የሚሉትን የሰብአዊ መብቶች መርሆችን ያከበሩ መሆናቸውን መንግሥት እንዲያረጋግጥ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።