በኢትዮጵያ ሰዎችን አስገድዶ መሰወር አሳሳቢ መሆኑን ኢሰመኮ ገለጸ
ድርጊቱ በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በስፋት እንደሚታይ ኮሚሽኑ አስታውቋል
ኢሰመኮ በሀገር አቀፍ ደረጃ አጥፊዎች አልያም ተጠርጣሪዎች በህግ ማዕቀፍ ብቻ እንዲዳኙ ጠይቋል
በኢትዮጵያ ሰዎችን ማፈን እና መሰወር አሳሳቢ መሆነቸውን ኢሰመኮ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች እየጨመረ የመጣውን የአስገድዶ መሰወር እና ተይዘው የሚገኙበት ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ጉዳይ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።
በተለይም ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በተከሰተባቸው የአዲስ አበባ ከተማ፣ የኦሮሚያ ክልል እና የአማራ ክልል ኮሚሽኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ኃላፊዎች በማነጋገር፣ በልዩ ልዩ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታዎች በመዘዋወር እና ከቤተሰቦችና ከሌሎች የመረጃ ምንጮች መረጃዎችን ማሰባሰቡን አስታውቋል።
አንድን ሰው የሚገኝበት ቦታና ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር መያዝ ማለት በተለይ በከባድ ወንጀል ተጠርጥሯል የተባለን ሰው ለወንጀል ምርመራ በሚል ምክንያት ከቤተሰብ እና ከጠበቃ እንዳይገናኝ አድርጎ በእስር የማቆየትን ተግባር የሚገልጽ ፅንሰ ሐሳብ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኢሰመኮ በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከደረሱት አቤቱታዎችና ጥቆማዎች በመነሳት ሲያደርግ በነበረው ክትትል መሠረት በርካታ የአስገድዶ መሰወር ድርጊቶች መከሰታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏብ።
አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ የሲቪልና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታና ደኅንነት ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ስፍራ እየተወሰዱ እንዲሰወሩ ተደርገዋልም ተብሏል።
ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ወራት መሰወር በኃላ የተገኙ መሆናቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ ሌሎች ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ በግዳጅ እንደተሰወሩ መቀጠላቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ከተጎጂዎች መካከል የተወሰኑት ሲያዙ በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ መሆኑ ተነግሯቸው ወደ መደበኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ የተሰወሩ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ምንም ሳይነገራቸው በጸጥታ ኃይሎች ተወስደው የተሰወሩ ናቸው ተብላል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በማስገደድ ተሰውረው ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ከተለያየ የጊዜ መጠን መሰወር በኃላ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው የተገኙ ሲኖሩ፣ አስገድደው በተሰወሩበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ ገላን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የቀድሞው ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ ተይዘው እንደቆዩ ተረድቻለሁም ብሏል ኮሚሽኑ።
በአስገድዶ መሰወሩ ወቅት ተፈጽሟል ስለተባለ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ወይም የማሰቃየት ተግባር ኮሚሽኑ ምርመራውን መቀጠሉን ገልጾ የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀ ትክክለኛውን ሁኔታ እንደሚገልጽ አስታውቋል።
በአማራ ክልል በባሕር ዳር እና በደብረ ብርሃን ከተማ የአስገድዶ መሰወር ሰለባዎች የሆኑ ሰዎችን ጉዳይ ኮሚሽኑ ሲከታተል ቆይቶ የነበረ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ አንድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ከሠራዊቱ ከድቷል በሚል በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ወረብ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወላጅ አባቱን ልጅህን አምጣ በሚል ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በግዳጅ ተወስደው ተሰውረው ከቆዩ በኋላ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም መለቀቃቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል ፡፡
አንድ የቀድሞ የሶማሊ ክልል ልዩ ኃይል አባል ታኅሣሥ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ከቢሮ ተደውሎለት ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሮ እንዲመጣ ተጠርቶ ከሄደ በኋላ በዕለቱ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጅምሮ ስልኩ የተዘጋ ሲሆን፣ ከዚያ ቀን ጀምሮ የት እና ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ማወቅ አለመቻሉን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ቢያንስ ሰባት ሰዎች የአስገድዶ መሰወር ድርጊት ሰለባ መሆናቸው ለኢሰመኮ አቤቱታ ቀርቦ ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጿል።
ከነዚህ መካከል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በወረዳው ፖሊስ ከሌሎች ሦስት ጓደኞቹ ጋር ተይዞ ፖሊስ ጣቢያ ከገባ በኋላ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሌሎቹ ታሳሪዎች ተለይቶ ነቀምት ከተማ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መዘዋወሩ ለቤተሰብ የተነገረ ቢሆንም ከዚያ ቀን ጀምሮ ያለበትን ቦታ እና ሁኔታ ማወቅ አልተቻለም፡፡
በተመሳሳይ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የምሥራቅ ወለጋ ዞን የኦፌኮ አስተባባሪ የሆነ ሌላ ሰው ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት በመንግሥት የደኅንነት ኃይሎች ተይዞ ነቀምት ከተማ በሚገኘው የጸጥታ ቢሮ ውስጥ ታስሮ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶበት እንደነበረና እጁ በሰንሰለት በመታሰሩ ምክንያት ከቤተሰብ የሚሄድለትን ምግብ ተቀብሎ መመገብ ሲያቅተው ሰዎች የተመለከቱት መሆኑን ከመረጃ ምንጮች ማወቅ መቻሉን እና ከጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሊገኝ አልቻለም ሲል ኮሚሽኑ ገልጿል።
ከተጎጂዎች መካከል የተወሰኑት መጀመሪያ ከተመዘገቡበት ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱት ከመደበኛው የተጠርጣሪ እና የእስረኛ የዝውውር ሂደት ውጪ እና በምሽት በመሆኑ ፍለጋቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገውም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
ቡራዩ ከተማ በተለምዶ አሸዋ ሜዳ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊሶች ተይዞ በቡራዩ ወረዳ 3 ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ውሎ የቆየ አንድ ሰው ከሁለት ወራት የፖሊስ ጣቢያ ቆይታ በኋላ አንድ ቀን ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ ከሌሎች እስረኞች ተለይቶ መወሰዱ የታወቀ ቢሆንም ፣ ከዚያን ቀን ጀምሮ ያለበትን ቦታ እና ሁኔታ ማወቅ አልተቻለም፡፡
ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ ቁጥራቸው ከሃያ ያላነሱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሱሉልታ ወረዳ፣ ለገሄጦ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር፣ ልዩ ስሙ ረቡዕ ገበያ፣ 04 ቀበሌ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ በመምጣት አንድ ሰው ይዘው የሄዱ ሲሆን፤ በማግስቱ ቤተሰቦቹ ታሳሪውን ለመፈለግ ወታደሮቹ ይኖሩበት ወደነበረው ደርባ ቶኒ፣ አበባ ልማት ካምፕ ቢሄዱም ወታደሮቹ የተያዘው ግለሰብ ያለበትን ሁኔታ ሊያሳውቁ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን፤ ይልቁንም ለመጠየቅ የሄዱ ሰዎች እስር እና ማስፈራርያ የደረሰባቸው መሆኑን ለኮሚሽኑ እንደገለጹለት እና ይህ ግለሰብም እስከ አሁን ድረስ ያለበት ሁኔታ እና ቦታ ማወቅ አልተቻለም፡፡
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እጅግ ውስብስብ የሆነ የጸጥታና ደኅንነት ሥጋት፣ ዘርፈ ብዙ ወንጀሎች፣ በመንግሥትና የሕዝብ አገልጋዮች ላይ በሚፈጸም ጥቃትና ግድያ ፈታኝ የሆነ የወንጀል መከላከልና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሥራ መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ማናቸውም የወንጀል መከላከልና አጥፊዎችን የመቅጣት ሥራ ሙሉ በሙሉ በሕጋዊና ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ ሥርዓት ብቻ ሊመራ እንደሚገባው ኢሰመኮ አሳስቧል።