“አላዳንከኝም” በሚል ቀዶ ጥገና ያደረገለትን ዶክተር ጨምሮ ሶስት ሃኪሞችን የገደለው ታጣቂ
በአሜሪካ 390 ሚሊዮን ሽጉጦች በግለሰቦች እጅ እንደሚገኙ ይነገራል
ተጠርጣሪው ከቀዶ ጥገናው በኋላ ጨርሶ ባለመዳኑ ዶክተር ፊሊፕስን ሲወቅስ ነበር ተብሏል
በአሜሪካ ኦክላሆማ ቅዱስ ፍራንሲስ ሆስፒታል “አላዳነኝም” በሚል አንድ ታጣቂ በተኮሰው ጥይት ቀዶ ጥገና ያደረገለትን ጨምሮ ሶስት ሀኪሞች መግደሉ ተሰማ፡፡
ታጣቂው በፈጸመው ድርጊት፤ ቀዶ ጥገና ያደረጉለትን ዶክተር ፕረስተን ፊሊፕስን ጨምሮ ሌሎች ዶክተር ስቴፋኒ ሁሰን፣አማንዳ ግለን እና ዊልያም ላቭን የተባሉ የህክምና ባለሙያዎች መሞታቸውም ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪው ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ራሱን በጥይት ማጥፋቱም ነው የተገለጸው፡፡
ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ ወደ ሆስፒታሉ ሲገባ ኤአር-15 የተሰኘ ጠብመንጃ እና ሽጉጥ ይዞ እንደነበር ፖሊስ አረጋግጧል፡፡
የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ወንደል ፍራንክሊን፡ ተጠርጣሪው ግንቦት 19 ቀን 2022 በቅዱስ ፍራንሲስ በወገቡ ላይ ቀደ ጥገና ተደርጎለት የነበረና "ከቀዶ ጥገናው በኋላ ጨርሶ ባለመዳኑ ዶክተር ፊሊፕስን ሲወቅስ የነበር ነው" ብለዋል፡፡
ተጠርጣሪው ከሆስፒታል ከወጣ በኋላም ቢሆን "ለበርካታ ቀናት ወደ ዶክተሩ በመደወል ህመም እንዳለውና ተጨማሪ ህክምና እንደሚያስፈልገው ሲገልጽ እንደነበር” ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በዚህ የተነሳ ተጠርጣሪው ዶክተሩን ለመግደል ወደ ሆስፒታሉ እንደመጣ ከድርጊቱ በኋላ በተገኘው ደብዳቤ ፖሊስ ለመረዳት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አሳዛኝ ክስተቱን ተከትሎ የቅዱስ ፍራንሲስ ሆስፒታል መግለጫ ያወጣ ሲሆን በተፈጸመው ድርጊት እጅጉን ማዘኑ ገልጿል፡፡
በአሜሪካ 390 ሚሊዮን ሽጉጦች በግለሰቦች እጅ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ፤ እ.ኤ.አ ከ2020 ወዲህ በአሜሪካ በጥይት የሚፈጸሙ ወንጀሎች ቁጥር በሁለት እጥፍ ጨምረዋል፡፡
ባለፈው ወር በኒውዮርክ በሚገኘው ሱፐርማርከት እንዲሁም በቴክሳስ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የታጠቁ ግለሰቦች በፈጸሙት የቶክስ ወንጀል ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ዜጎች መሞታቸው አይዘነጋም፡፡