ከትራምፕ በፊት መሪ የነበሩት ባራክ ኦባማ በ2016 ኩባን ጎብኝተው ነበር
የጆ ባይደን አስተዳደር በኩባ ላይ ተጥሎ የነበረውን የበረራ ዕገዳ እንደሚያነሳ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ።
በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናል ትራምፕ አስተዳደር ዘመን በኩባ ላይ የበረራ እገዳ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም ዕገዳው እንዲነሳ ተወስኗል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኩባ ላይ የተጣለው የበረራ ዕገዳ እንዲነሳ ለሀገራቸው የትራንስፖርት መምሪያ በደብዳቤ አሳውቀዋል ተብሏል።
በዚህም መሰረት የአሜሪካ አውሮፕላኖች ወደ ኩባ ከተሞች እንዲበሩ ተፈቅዷል። የአሜሪካ አውሮፕላኖቿ ከኩባ መዲና ሃቫና በተጨማሪም ወደ ሌሎች አውሮፕላን ማረፊያዎች መብረር እንዲችሉ አሜሪካ በይፋ ፈቅዳለችም ነው የተባለው።
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአውሮፓውያኑ ታህሳስ 2019 ጀምሮ የሀገራቸው አውሮፕላች ከኩባ ዋና ከተማ ሃቫና ውጭ ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዳይበር እገዳ አስቀምጠው እንደነበር ይታወሳል።
ትራምፕ እገዳው እንዲጣል የወሰኑት የኩባ መንግስት፤ በኒኮላስ ማዱሮ የምትመራውን የቬንዙዌላን መንግስት ይደግፋል፤ አምባገነን መንግስት ነው በሚል መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።
ከትራምፕ በፊት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማ ደግሞ በመሪነት ዘመናቸው በኩባ እና በአሜሪካ መካከል ያለው የውጭ ግንኙነት እንዲሻሻል ለማድረግ እ.ኤ.አ መጋቢት 2016 የኩባን መዲና ሃቫናን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
በወቅቱ የኦባማ ምክትል የነበሩትና የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሀገራቸው ከኩባ ጋር ያላትን ግንኑነት ዕገዳ በማንሳት ጀምራለች።