አሜሪካ ማይክ ሀመርን በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ ሾመች
ብሊንከን “ከአምባሳደር ሀመር ጋር በቀጠናው የምናደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማስቀጠል እጓጓለሁ” ብለዋል
ዴቪድ ሳተርፊልድ ከአሁን ቀደም በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል
አሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድን በመተካት በአፍሪካ ቀንድ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ መሾሟን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አስታወቁ፡፡
አምባሳደር ማይክ ሀመር ናቸው ዴቪድ ሳተርፊልድን በመተካት በልዩ መልዕክተኛነት የተሾሙት፡፡
የማይክ ሃመርን መሾም በትዊተር ገጻቸው ይፋ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሊንከን፤ ሀመር አሜሪካ በቀጠናው የጀመረችውን ዲፕለማሲያዊ ጥረት እንደሚያስቀጥሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
ብሊንከን “ከአምባሳደር ሀመር ጋር በቀጠናው የምናደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማስቀጠል እጓጓለሁ”ም ነው ያሉት፡፡
ማይክል (ማይክ) ሀመር ቀደም ሲል በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ቺሊ አምባሳደር ሆነው አሜሪካን አገልግለዋል፡፡
የብሔራዊ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ደህንነት ጉዳዮች ኮሌጅ ምክትል ቻንስለር በመሆን ያገለገሉ አንጋፋ ዲፕሎማት መሆናቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ዴቪድ ሳተርፊልድ ከኃላፊነታቸው ሊለቁ እንደሚችሉ የዓለም አቀፍ ጉዳዮችና ግንኙነቶችን ትኩረት አድርጎ የሚዘግበው ፎሬይን ፖሊሲ ከሁለት ወራት በፊት ባወጣው መረጃ ማመላከቱ አይዘነጋም።
የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት ዴቪድ ሳተርፊልድ ከኃላፊነት መልቀቅ፤ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የጅምላ ግድያና የረሃብ ስጋት ባለበት ቀጠና ትልቅ የሆነ የዲፕሎማሲ ክፍተት የሚፈጥር እንደሆነም ሲገለጽ ነበር።
ፎሬይን ፖለሲ በወቅቱ ይህን ይበል እንጂ፤ ከሳተርፊልድ ከኃላፊነት መልቀቅ ጋር ተያይዞ ለምን እና መቼ በሚሉ ጊዳዮች ላይ ያለው ነገር እንዳለነበር እንዲሁም በአሜሪካ መንግስት በኩል ምንም ነገር ሳይባል መቆየቱ ይተወቃል፡፡