በጥቃቱ አምስት የአል ሸባብ ተዋጊዎች ተገድለዋ ተብሏል
አሜሪካ በሶማሊያ የመሸጉትንና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የአልሻባብ ተዋጊዎች ኢላማ ያደረገ የአየር ጥቃት ሰነዘረች፡፡
አሜሪካ የወሰደቸው እርምጃ፤ ጆ ባይደን ወታደሮቻቸውን እንደገና ወደ አፍሪካ ቀንዷ ሀገረ ሶማሊያ እንደሚልኩ ካሳወቁ በኋላ የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ ነው፡፡
በጥቃቱ አምስት የአልሸባብ ተዋጊዎች መገደላቸውን እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ገልጿል። ሆኖም ዋሽንግተን ወሰደችው ስለተባለው እርምጃ እስካሁን ያለችው ነገር የለም፡፡
አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አልሸባብ በሚያሰጋ ሁኔታ እየጠነከረ መጥቷል፡፡
ለዚህም ከ500 ያላነሱ ከሶማሊያ ውጭ ሲሰሩ የነበሩ የአሜሪካ ልዩ ኦፕሬተሮች ወደ ሶማሊያ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን የቀጠናው ስጋት የሆነውን አልሻባብ ለመምታት 600 የሚሆኑ የሃገራቸውን ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንደሚልኩ ባለፈው ወር ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
የአሜሪካ ጦር በድጋሚ በሶማሊያ እንዲሰማራ የማድረግ ውሳኔ በ10ኛው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ተቀባይነት ማግኘቱም አይዘነጋም፡፡
ሶማሊያ አሁንም በአልሻባብ እየተፈተነች ነው። በተለይም ከምርጫ ጋር በተያያዘ በሃገሪቱ ፖሊተከኞች መካከል የነበረው ሽኩቻ ለሰላምና ጸጥታ ይሰጥ የነበረውን ትኩረት አላልቶት እንደነበር በርካቶች ያነሳሉ።
የአሁኑ የአሜሪካ እርምጃም ቡድኑን ከማዳከም አንጻር ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተነግሮለታል፡፡
የፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ጽ/ቤትም "ለመረጋጋትና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በምናደርገው ትግል አሜሪካ ወትሮም ቢሆን ታማኝ አጋራችን ናት" የሚል ጽሁፍን በትዊተር ገጹ አጋርቷል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አልሻባብ ተዳክሟል በሚል 700 የአሜሪካ ጦር አባላት ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የአልሻባብ የሽብር ድርጊት እየጨመረ መጥቷል በሚል የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ በባይደን ተሽሯል።
ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ፤ መሃመድ አብዱላሂ መሃመድ (ፋርማጆ)ን ተከትው በቅርቡ በሶማሊያ ፕሬዝዳንትነት በድጋሚ መመረጣቸው ይታወሳል፡፡