የሀጫሉ ሁንዴሳ “ማል መሊሳ” አለበም በአይቱንስ ወርልድ ቻርት ሽያጭ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል
አልበሙ በሀገር ውስጥ የኢንተርኔት የሙዚቃ መሸጫ በሆነው “አውታር” ላይም በ1ኛ ደረጃ እየተሸጠ ይገኛል
“ማል መሊሳ” አለበም በሲዲ ደረጃ 300 ሺህ ኮፒ ታትሞ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተሰራጭቷል
አዲሱ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ “ማል መሊሳ (Maal Mallisaa) የሙዚቃ አልበም በዓለም አቀፉ የኢንተርኔት የሙዚቃ መሸጫ በአይቱንስ ወርልድ ቻርት ሽያጭ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ 3ኛ የሙዚቃ አልበም የሆነው“ማል መሊሳ (Maal Mallisaa) የሙዚቃ አልበም ባሳለፍነው ሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ለገበያ መቅረቡ ታውቋል።
የአልበሙ የሽያጭ አስተባባሪ አቶ አመንሲሳ ኢፋ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናሩት አልበሙ በሲዲ እንዲሁም በተለያዩ የኢንተርኔት የሙዚቃ ማሻሻጫ ድረ-ገጾች አማካኝነት ለገበያ ቀርቧል፡፡
ሙዚቃው ለዓለም አቀፍ ገበያ ከተለቀቀባቸው በይነ መረቦች ውስጥ አይቱንስ አንዱ ሲሆን፤ ሙዚቃው በአይቱንስ የሽያጭ ሰንጠረዥ ላይ ከዓለም 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
አልበሙ እስከ ትናንት ባለ መረጃ በተለቀቀ በሁለት ቀናት ውስጥ ነው በአይቱንስ ወርልድ ቻርት ሽያጭ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለው።
“ማል መሊሳ” አለበም በአይቱንስ በሀገራት ባለው ሽያጭ ያለው ደረጃ ሲታይም በአውስትራሊያ፣ በካናዳ እና በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች 1ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በአሜሪካ በ2ኛ ደረጃ ላይ፣ በብሪታንያ 9ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም በበርካታ ሀገራት እስከ 10 ባሉ ደረጃዎች ላይ መቀመጥ መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአይቱንስ ወርልድ የሙዚቃ ሽያጭ ሰንጠረዥ በየሰዓቱ የሚለዋወጥ ሲሆን፤ የሙዚቃው የሽያጭ ደረጃ ሊጨምር አሊያም ሊቀንስ ይችላል።
“ማል መሊሳ” አልበም በሀገር ውስጥም በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸጠ መሆኑን የአልበሙ የሽያጭ አስተባባሪው አቶ አመንሲሳ ተናግረዋል። አልበሙ በሀገር ውስጥ የኢንተርኔት የሙዚቃ መሸጫ በሆነው “አውታር” ላይ በ1ኛ ደረጃ እየተሸጠ እንደሆነም አቶ አመንሲሳ ተናግረዋል።
“ማል መሊሳ” አለበም በሲዲ ደረጃ 300 ሺህ ኮፒ ታትሞ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች መሰራጨቱን እና አንዱ ሲዲ በ100 ብር እየተሸጠ ነው ያስታወቁት።
አዲሱ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ “ማል መሊሳ (Maal Mallisaa) የሙዚቃ አልበም አልበሙም 14 ዘፈኖችን ያካተተ ሲሆን በሳለፍነው ሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል መመረቁ ታወሳል።
ከአልበም ምርቃቱ ጎን ለጎንም የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ 1ኛ ሙት አመት መታሰቢያ የተካሄደ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለአርቲስቱ መታሰቢያ ያቆመለትን ሀውልት በዕለቱ ይፋ አድርጎ፤ በቅርቡ እንደሚመረቅ መግለጹ ይታወሳል።
አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ ገላን ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በጥይት ተመትቶ ህይወቱ ማለፉም ይታወሳል።