ከአርቲስት ሀጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ሁከት 4.6 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙ ተገለጸ
በሁከቱ የ160 ሰዎች ህይወት እንዳለፈ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል
ሁከቱን በመቀስቀስ እና በሁከቱ በመሳተፍ ከተጠረጠሩት መካከል በ2,000 ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቷል
ከአርቲስት ሀጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ሁከት 4.6 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙ ተገለጸ
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር በተለይ ባለፉት 3 ወራት የተወሰዱ ሕጋዊ እርምጃዎችን በተመለከተ በዛሬው ዕለት መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ሁከት በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት እና የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ አብራርተዋል፡፡
ዐቃቤ ሕጉ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በሁከቱ 160 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን እና 360 ሰዎች ደግሞ ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
አጠቃላይ በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳትም 4.6 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት ነው ዶ/ር ጌዲዮን የገለጹት፡፡
ሁከቱን በመቀስቀስ እና በሁከቱ በመሳተፍ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሰዎች መካከል ፖለቲከኞችን ጨምሮ በ2,000 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱንም ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ አብራርተዋል፡፡
የሁከት ድርጊቱ በሰኔ ወር መገባደጃ ላይ ከተፈጸመ በኋላ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል በሐምሌ ወር አጠቃላይ የማጣራት ስራ ተከናውኖ በነሐሴ እና አሁን በምንገኝበት የመስከረም ወር ላይ ደግሞ ክስ መመስረቱን በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡
ዶ/ር ጌዲዮን እንዳሉት የተጠርጣሪዎችን ጉዳይ የማጣራቱ እና ክስ የመመስረቱ ጉዳይ መዘግየት የተስተዋለበት ወንጀሉ ሰፊ ቦታ የሚሸፍንና ዉስብስብ ከመሆኑ በተጨማሪ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ መንግሥት ተቋማትን እንደ አዲስ በመገንባት ሂደት ላይ በመሆኑም ነው፡፡
ማንም ግለሰብ በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት በቁጥጥር ስር እንዲውል እንዳልተደረገ እና በቁጥጥር ስር ዉለው ክስ የተመሰረተባቸው ሁሉም ግለሰቦች ፈጽመዋል በተባለው ጥፋት ብቻ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መግለጫ ወቅት የጽ/ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም መንግስት ቀጣዩን ምርጫ ሰላማዊ እና ተዓማኒ በሆነ መንገድ እንዲከናወን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ እየተከናወኑ የሚገኙ እና የታቀዱ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ካለፉት አፈጻጸሞች ተሞክሮ በመውሰድ በትጋት የማከናወን እንዲሁም በሀገሪቱ ሕግና ስርዓትን የማስከበር ተግባራትም በከፍተኛ ትኩረት እነደሚሰራባቸው አንስተዋል፡፡