ከሳምንታት በፊት ፕሬዝዳንቷን በግድያ ያጣችው ሄይቲ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመች
ፕሬዝዳንት ጆቬናል ሞይስ እ.ኤ.አ ከ2017 ጀምሮ እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ ሃገራቸውን አገልግለዋል
አዲሱ ጠ/ሚ ሃገሪቱን የሚመራ መንግስት በስምምነት እንደሚመሰርቱ ቃል ገብተዋል
ፕሬዝዳንት ጆቬናል ሞይስን ከሳምንታት በፊት በግድያ ያጣችው ሄይቲ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመች፡፡
አሪዬል ሄንሪ በባለደራነት ሃገሪቷን ለጊዜው ሲመሩ የነበሩትን ክላውድ ጆሴፍን ተክተው በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡
አዲሱ ጠ/ሚ አሪዬል ሄንሪ የነርቭ ቀዶ ጥገና ሐኪም እና የካቢኔ ሚኒስትር የነበሩ ናቸው፡፡
ውስብስብ እና ከባድ የቤት ስራዎች እንደሚጠብቋቸው በበዓለ ሲመታቸው ወቅት የተናገሩት ሲሆን ለሃገራዊ አንድነት ጥሪ አቅርበው ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ውይይትን ከተለያዩ አካላት ጋር ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ሃገሪቱን የሚመራ መንግስት በስምምነት እንደሚመሰርቱም ቃል በመግባትም ነባር የካቢኔ አባላትን ያካተተ አዲስ ካቢኔ አስተዋውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ጆቬናል ሞይስ ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር ‘ቅጥረኞች ናቸው’ በተባሉ ጥቃት ፈጻሚዎች የተገደሉት፡
ሆኖም ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ማርቲን ሜሪ ጭምር ከተጎዱበት ጥቃት ጀርባ ማን ያለው ማነው ስለሚለው እስካሁን የታወቀ ግልጽ ነገር የለም፡፡
ከግድያው ጋር በተያያዘ የሃገሪቱ ፖሊስ እጃቸው እንዳለበት ጠርጥሬያቸዋለሁ ያላቸውን በትንሹ 26 ሰዎችን መያዙን አስታውቋል፡፡
ከተያዙት መካከል 18ቱ የቀድሞ የኮሎምቢያ ጦር አባላት፣5ቱ ሃይቲያውያን እና 3ቱ ደግሞ ሃይቲ-አሜሪካውያን ናቸው፡፡
በሃገሪቱ ፖሊስ ውስጥ ሰርጎ ገብ አካላት እንዳሉ የገለጹት የፖሊስ ባለስልጣናት ተጨማሪ ሶስት አባላት መያዛቸውንም ገልጸዋል፡፡
ስራ ፈጣሪው ፕሬዝዳንት ሞይስ ሄይቲን ላለፉት 5 ዓመታት አገልግለዋል፡፡