ሀማስ አጋሩ ሄዝቦላ ከእስራኤል ጋር ስለደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ምን አለ?
እስራኤል እና ሄዝቦላ በፈረንሳይ እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ተኩስ ለማቆም ከተስማሙ በኋላ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል
ሀማስ ሊባኖስ ህዝቧን ለመከላከል ስትል ያደረገችውን ስምምነት እንደሚያከብር ገልጿል
የሀማስ ባለስልጣን የሆኑት ሳሚ አቡ ዙህሪ ቡድኑ ሊባኖስ ህዝቧን ለመከላከል ስምምነት የማድረግ መብቷን እንደሚያከብር እና የጋዛውን ጦርነትም የሚያስቆም ስምምነት እንደሚደረስ ተስፋ እንደሚያደርግ በዛሬው እለት ተናግሯል።
እስራኤል እና ሄዝቦላ በፈረንሳይ እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ተኩስ ለማቆም ከተስማሙ በኋላ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል። ነገርግን በጋዛ በሃማሰ እና በእስራኤል መካከል ለ 13 ወራት ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም የተደረገው አለምአቀፍ ጥረት ቆሟል።
"ሀማስ ሊባኖስ እና ሄዝቦላ የሊባኖስን ህዝብ ለመከላከል ሲሉ የሚያደርጉትን ስምምነት ያከብራል፤ ስምምነቱ በጋዛ በህዝባችን ላይ እየተካሄደ ያለውን የዘርማጥፋት ጦርነት ለማስቆም በር እንደሚከፍት ተስፋ ያደርጋል" ሲል አቡ ዙህሪ ለሮይተርስ ተናግሯል።
ቡድኑ ረቡዕ ረፋድ ባወጣው መግለጫ ስምምነት ለማድረግ ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን አስታውሶ፣ ጦርነቱን ለማስቆም ለሚደረጉ ጥረቶች በሩ ክፍት መሆኑን ገልጿል።
"ስምምነት ላይ ለመድረስ ለሚደረጉ ጥረቶች ለመተባበር ዝግጁ ነን።በህዝባችን ላይ የሚረገውን ወረራ ለማስቆም ፍላጎት አለን" ብሏል ሀማስ።
ሀማስ አክሎም እንደገለጸው ሊኖር የሚችለው ስምምነት ጦርነቱን የሚያስቅም፣ የተፈናቀሉ ጋዛውያንን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚያስችል፣ የእስራኤልን ጦር ከጋዛ የሚያስወጣ እና የታጋቾችን እና የእስረኞችን ልውውጥ የሚያሳካ መሆን አለበት።
በጋዛ ተመሳሳይ ስምምነት ባለመደረሱ አብዛኞቹ ነዋሪዎች ችላ ተብለናል የሚል ስሜት አድሮባቸዋል። የእስራኤል ጦር በዛሬው እለት በጋዛ በፈጸመው የአየር ጥቃት 15 ሰዎች መገደላቸውን የጤና ባለሙያዎች ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
ኳታር እስራኤል እና ሀማስ ለእውነተኛ ድርድር ያላቸውን ፍላጎት እስከሚያሳዩ ድረስ ማደራደሯን ማቆሟን ካሳወቀች በኋላ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ለበርካታ ወራት ሲደረግ የቆየው ጥረት ባለበት ቆሟል።
አቡ ዙህሪ ለተኩስ አቁም ስምምነቱ አለመሳካት የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ወቅሰዋል። ኔታንያሁም ለስምምነቱ አለመሳካት ሀማስን ተጠያቂ ሲያደርጉ ይደመጣሉ።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረስ አስተዳደራቸው ከቱርክ፣ ግብጽ እና ኳታር ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።