እስራኤል እና ሄዝቦላ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ባይደን አስታወቁ
በእስራኤል እና ሄዝቦላ መካከል ለ 13 ወራት ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት የሚያስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸሙን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስታውቀዋል
እስራኤል ሄዝቦላ ስምምነቱን የሚጥስ ከሆነ የምላሽ የመስጠት መብት እንዳላት ገልጻለች
እስራኤል እና ሄዝቦላ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ባይደን አስታወቁ።
በእስራኤል እና ሄዝቦላ መካከል ለ 13 ወራት ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት የሚያስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸሙን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስታውቀዋል።
በዛሬው እለት በአካባቢው ሰአት አቆጣጠር (02:00 GMT)በመላው ሊባኖስ የተኩስ ድምጽ እንደሚቆም የተናገሩት ባይደን ስምምነቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያለመ ነው ማለታቸው ተዘግቧል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሄዝቦላ ስምምቱን የሚጥስ ከሆነ እስራኤል ጥቃት ከመፈጸም ወደ ኋላ አትልም ብለዋል። ሀማስ በእስራል ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ከጥቅምት 7፣2023 ጀምሮ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ሲያስወነጭፍ የቆየው ሄዝቦላ እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።
በሁለቱ መካከል የነበረው ውጊያ ከፍተኛ ጡዘት ላይ የደረሰው እስራኤል ከፍተኛ የአየር ጥቃት ባደረሰችበት እና ሊባኖስን በእግረኛ ጦር በወረረችበት ባለፈው መስከረም ወር ነው።
የሊባኖስ ባለስልጣናት እንደገለጹት በአስርት አመታት ውስጥ አውዳሚ ነው ባሉት ጦርነት 3823 ሰዎች ተገድለዋል። የተኩስ አቁም በታቀደው መሰረት ተግባራዊ እየሆነ ነው።
የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሊደረስ ትንሽ ሲቀር በሁለቱም በኩል ጥቃቶች ተመዝግበዋል። እስራኤል ስምምነቱ ከመደረሱ ከአራት ሰአታት በፊት በተወሰነ የቤይሩት ከተማ ክፍል ሰዎች ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ አሰምታ ነበር። ሄዝቦላ በበኩሉ ጦርነት ሊቆም አንድ ሰአት ሲቀረው በእስራኤል ላይ የድሮን ጥቃት ፈጽሟል።
በአሜሪካ አደራዳሪነት ትናንት ምሽት በተደረሰው የ60 ቀናት ስምምነት መሰረት እስራኤል ቀስበቀስ ጦሯን ከደቡብ ሊቢኖስ የምታስወጣ ሲሆን የሊባኖስ ጦር አሁን በሄዞቦላ የተያዘውን ቦታ ይቆጣጠራል።
የሄዝቦላ ተዋጊወች እና የጦር መሳሪያ በ2006 ከተካሄደው የእስራኤል- ሊባኖስ ጦርነት በኋላ ድንበር ከሆነው ከላታኒ ወንዝ ደቡባዊ አካባቢ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
"ይህ ዜና ዘላቂ ሰላም የሚፈጥር እና በሁለቱም ሀገራት በኩል የተፈናቀሉ ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የሚያስችል ነው" ሲሉ የተኩስ አቀሙን ተግባራዊነት የሚከታተሉት አሜሪካ እና ፈረንሳይ ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል።
እስራኤል ሄዝቦላ ስምምነቱን የሚጥስ ከሆነ የምላሽ የመስጠት መብት እንዳላት ገልጻለች።
ፕሬዝደንት ባይደንም "እስራኤል አለምአቀፍ ህግን በመከተል ራሷን የመከላከል መብት አላት" በማለት አስተጋብተዋል።
"ሄዝቦላ ስምምነቱን ጥሶ ራሱን ለማስታጠቅ የሚሞክር ከሆነ ጥቃት እንፈጽማለን። በድንበር አካባቢ የሽብር መሰረተልማት የሚገነባ ከሆነ እናጠቃለን" ብለዋል ኔታንያሁ።
ኔታንያሁ እስራኤል በሰሜናዊ ጎረቤቷ ከሚንቀሳቀሰው ሄዝቦላ ጋር ስምምነት መፍጠሯ የእስራኤል ጦር ትኩረቱን በኢራን ላይ ብቻ እንዲያደርግ እንደሚያስችለው ገልጸዋል። ሄዝቦላ የቀጣናው የኢራን ጠንካራ አጋር ተደርጎ የሚወሰድ ቡድን ነው። ነገርግን በእስራኤል ጥቃት አብዛኞቹ የጦር መሳሪያዎቹ ወድመዋል፤ አመራሮቹም ተገድለዋል።
ኔታንያሁ እንዳሉት ስምምነቱ እስራኤል በተናጠል በሀማስ ላይ ጫና እንድታደርስ ይጠቅማታል።
ፕሬዝደንት ባይደን በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረስ አስተዳደራቸው ከቱርክ፣ ግብጽ እና ኳታር ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።