በአፍሪካ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 35 ሚሊዮን መሻገሩን ሪፖርት አመላከተ
ናይጄርያ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ በርካታ ተፈናቃዮች ከሚገኙባቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ
ከዚህ ውስጥ 93 በመቶ የሚሆኑ በግጭት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ናቸው
በግጭት፣ በጦርነት እና በተፈጥሮ በአደጋ ምክንያት የአፍሪካ መፈናቀል በሶስት እጥፍ መጨመሩን አዲስ ሪፖርት አመልክቷል።
መቀመጫውን በጄኔቫ ያደረገው የሀገር ውስጥ መፈናቀል መከታተያ ማዕከል ባወጣው ሪፖርት በአፍሪካ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በሶስት እጥፍ አድጎ 35 ሚሊዮን ደርሷል ብሏል።
ማዕከሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ከተፈናቀሉ ሰዎች ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ በአፍሪካ እንደሚገኙ ጠቅሶ ከእነዚህ ውስጥ 32.5 ሚሊዮን (93 በመቶ) የሚሆኑት በግጭት እና ብጥብጥ ምክንያት ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡
ሪፖርቱ ከ 2009 እስከ 2023 አዳዲስ የመፈናቀል አዝማሚያዎችን እና እድገቶች እየታዩ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ በአፍሪካ ከሚገኙ አጠቃላይ 35 ሚሊዮን ተፈናቃዮች 26 ሚሊየን የሚሆኑት በአምስት ሀገራት ማለትም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ተፈናቅለዋል ነው ያለው።
ድህነት፣ ኢ ፍትሀዊነት እና መገለል ግጭቶችን እንዲሁም ብጥብጦችን ከሚጨምሩ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ ያሉት ባለሙያዎች፣ የታጠቁ ሃይሎችም እነዚህን ቅሬታዎች በመጠቀም ተጨማሪ ግጭት እና መፈናቀልን መፍጠራቸውን አመላክተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ መፈናቀል መከታተያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አሌክሳንድራ ቢላክ "በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ አምስት ሀገራት ከግጭት ጋር የተያያዘ የውስጥ መፈናቀል እየፈጠሩ ይገኛሉ፤ ነገርግን ሪፖርታችን የአደጋ መፈናቀልም እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል ፤ በአሁኑ ወቅት ከ15 አመታት በፊት ከነበረው በስድስት እጥፍ የተፈጥሮ አደጋ መፈናቀል ጨምሯል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጎርፍ እና ድርቅ አብዛኞቹን የአደጋ መፈናቀል የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መባባስ እነዚህን ከአየር ሁኔታ ጋር የተያያዙ መፈናቀሎች የበለጠ ተደጋጋሚ እና ቀጣይ እንደሚያደርጋቸው ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ እና በዲር ኮንጎ የሚገኙ ግጭቶች አሁንም ድረስ መቀጠላቸው የዜጎችን ህይወት አስከፊ እንዲሆን ካደረጉ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ጥናቱ የአፍሪካ መንግስታት ግጭትን ለማስቀረት እና ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ ቢሆንም አሁን ላይ ከሚታዩ የተፈናቃይ ቁጥር አንጻር ቀሪ የቤት ስራዎች መኖራቸውን አመላካች ነው ብሏል፡፡