ሃማስ “እንደ ፊኒክስ ወፍ ከአመድ ውስጥ ነፍስ ዘርቶ ይነሳል” - ካሌድ መሻል
በስደት ላይ የሚገኙት የፍልስጤሙ ቡድን ከፍተኛ አመራር ሃማስ አዳዲስ ተዋጊዎችን እየመለመለ የጦር መሳሪያዎችንም እያመረተ ነው ብለዋል
እስራኤል ሃማስ ድንበሯን ጥሶ ድንገተኛ ጥቃት ያደረሰበትን አንደኛ አመት አስባ ውላለች
ሃማስ በእስራኤል ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት ቢያስተናግድም “እንደ ፊኒክስ ወፍ ነፍስ ዘርቶ ይነሳል” አሉ የቡድኑ ከፍተኛ አመራር ካሌድ መሻል።
በግሪክ አፈታሪክ “ፊኒክስ ወፍ” ተቃጥሎ ከሞተ በኋላ ከአመድ ውስጥ ራሱን ዳግም የሚወልድ እንደሆነ ይታመናል።
በስደት ላይ የሚገኙት የሃማስ ከፍተኛ መሪ ካሊድ መሻልም ሃማስ በእስራኤል የሚደርስበት ከባድ ጥቃት ቡድኑን ለዳግም ውልደትና ጥንካሬ ቢያበቃው እንጂ እንደማያጠፋው ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ፍልስጤማውያን ከ”ናቅባ” ወይም “መቅሰፍት” ጀምሮ ለ76 አመታት ያሳለፉት ታሪክ ተመሳሳይ ኡደት ያለው መሆኑን ነው ያብራሩት።
“ሰማዕታት እና ወታደራዊ አቅማችን የሚያሳጡ በርካታ ምዕራፎችን አልፈናል፤ ይሁን እንጂ በነዚህ ሂደቶች ሁሉ የፍልስጤማውያን የተጋድሎ መንፈስና ለሞት አይበገሬነት እንደ ፊኒክስ ወፍ እየሆነ ቀጥሏል” ሲሉም ያክላሉ።
በፈረንጆቹ 1997 የእስራኤልን የመርዝ ግድያ ሙከራ ያመለጡት መሻል፥ ከ1996 እስከ 2017 ድረስ የሃማስ መሪ ሆነው አገልግለዋል።
በሃማስ አመራር ውስጥ ለሶስት አስርት አመታት የዘለቁት ካሌድ መሻል በቡድኑ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ግለሰቦች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሃማስ በ12 ወራት ያላባራ የእስራኤል ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱን የማይክዱት መሻል፥ ይሁን እንጂ አሁንም እስራኤል ላይ ጥቃት ማድረስ የሚያስችል አቅም እንዳለው አብራርተዋል።
ቡድኑ አዳዲስ ተዋጊዎችን እየመለመለ የጦር መሳሪያዎችንም በብዛት እያመረተ መሆኑን በመግለጽም ጦርነቱ ቀጣይነቱን የሚያመላክት አስተያየት ሰጥተዋል።
እስራኤል ሃማስ ድንበሯን ጥሶ ድንገተኛ ጥቃት የፈጸመበትን አንደኛ አመት በትናንትናው እለት አስባ ውላለች። በርካታ ዜጎችም በጋዛ የሚገኙ እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ሃማስ በበኩሉ ከጋዛ ወደ እስራኤል አራት ሚሳኤሎችን በመተኮስ አለሁ የሚል መልዕክቱን አስተላልፏል።
እስራኤል በአንድ አመት የአየር እና የምድር ጥቃቷ የሃማስ ወታደራዊ መዋቅር ፈራርሶ ወደ ተራ ሽምቅ ተዋጊነት መውረዱን ታምናለች።
በፍልስጤም ከተመዘገበው ከ42 ሺህ ሞት ውስጥ 17 ሺህ የሚጠጉት የሃማስ ተዋጊዎች መሆናቸውንም ትገልጻለች።
እስራኤል በሃማስ ተዋጊዎች ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰች ከመናገር የተቆጠቡት ካሌድ ማሻል፥ የኔታንያሁ አስተዳደር በስልጣን ላይ እያለ በጋዛ ሰላም አይሰፍንም ብለዋል።
“እስራኤል በጋዛ ወረራዋ እስከቀጠለ ድረስ ቀጠናው በስአት የሚፈነዳ ቦምብ ነው” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።