እስራኤል ጋዛን ድጋሚ ለኑሮ እንዳይመች አድርጋ አውድማዋለች- ሙሀሙድ አባስ
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት በመንግስታቱ ድርጅት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር መላው አለም በጋዛ እየሆነ ላለው ተጠያቂ ነው ብለዋል
የእስራኤል ጦር በአፋጣኝ ከጋዛ እንዲወጣ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያሳደር ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋ
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ሙሀሙድ አባስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጋዛውን ጦርነት በአስቸኳይ እንዲያስቆም ጥሪ አቀረቡ፡፡
ፕሬዝዳንቱ በመንግስታቱ ድርጅት 79ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ድርጅቱ የንጹሀንን ሞት በማስቆም ፣ የሀገራትን ነጻነት ማስጠበቅ እና ሰላምን ማስፈን የመሳሰሉ ድርጅቱ የተቋቋማባቸውን አላማዎች ማስፈጸም ላይ ውድቀት ደርሶበታል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
እስራኤል ከሀማስ ጋር በገባችበት ጦርነት ጋዛን ድጋሚ ለመኖር እንዳይመች አድርጋ አውደመዋለች ያሉት አባስ ይህ “እብደት” ከዚህ በላይ ሊቀጥል አይገባም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
193 አባላት ላሉት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር መላው አለም በጋዛ ለሆነው እና እስካሁን ለቀጠለው ስቃይ ተጠያቂ ነው በሚል ወንጅለዋል፡፡
የጥቅምት ሰባቱን የሃማስ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል የከፈተችው ውግያ እያበቃ እንደሆነ የሚያመላክቱ ምልክቶች እስካሁን አልታዩበትም፡፡
አሜሪካ የጸጥታው ምክር ቤት ምዕራባውያን እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀያላን ጦርነቱ እንዲቆም የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግጭቱ የንጹሀንን ሞት እየቀጠፈ መቀጠሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እና ርሀብ በተንሰራፋበት ጋዛ እስካሁን በጦርነቱ ከ41 ሺህ በላይ ንጹሀን ሲገደሉ ከ 2.3 ሚሊየን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡
ሙሀሙድ አባስ ሁሉን አካታች ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈጸም የጠየቁ ሲሆን በዌስት ባንክ የእስራኤል ዜጎች በፍልስጤማውያን ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙ ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ እና ሰብአዊ እርዳታዎች ያለምንም እንቅፋት እንዲሰራጩ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጽእኖውን እንዲያሳድር ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
ከጋዛ አንድ ሴንቲ ሜትር እንዲወስድ አንፈቅድም ያሉት ፕሬዝዳንቱ እስራኤል የመከላከያ ዞኖችን በጋዛ ድንበሮች አቅራቢያ አቋቁማለሁ ማለቷንም እንደማይቀበሉ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሁሉም የፍልስጤም ግዛቶች በፍልስጤም አስተዳደር እንጂ ከውጪ በመጣ አካል አይጠበቁም ሀላፊነቱም የአስተዳደሩ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ለፕሬዝዳንቱ ንግግር በሰጡት ምላሽ ሙሀሙድ አባስ የጋዛውን ጦርነት የቀሰቀሰውን የጥቅምት ሰባቱን ጥቃት ሳያዋግዙ ሰለሰላማዊ አማራጭ ማውራታቸው መታበይ ነው በሚል ነቀፌታቸውን ገልጸዋል፡፡