የእስራል እና ሀማስ ጦርነት በአንድ አመት ውስጥ ሲቃኝ
ሀማስ ጥቅምት 7 በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ የጀመረችው ጥቃት ዛሬ አንድ አመቱ ነው
እስራኤል በጦርነቱ ከ40 ሺ በላይ የሀማስ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ፈጽማ ከአጠቃላይ የቡድኑ ታጣቂዎች ግማሽ ያህሉን መደምሰሷን ይፋ አድርጋለች
የእስራል እና ሀማስ ጦርነት በአንድ አመት ውስጥ ሲቃኝ
አንድ አመት ያስቆጠረው የጋዛ ጦርነት በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አስከትሏል፡፡
ጦርነቱ 42 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማዊያንን ህይወት ሲነጥቅ 2 ሚሊየን የሚሻገሩ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሀማስ ጥቅምት ሰባት በፈጸመው ጥቃት ከ250 በላይ ሰዎችን ሲያግት 1200ዎቹ ደግሞ ገድሏል።
ከሀማስ ጋር ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ጦርነቱ እንዲያበቃ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያድርግም መሳካት አልቻለም፡፡
በተለይ በአሜሪካ የቀረበው የተኩስ አቁም እና የድህረ ጦርነት የስምምነት ሀሳብ ግብጽ እና ኳታር ተጨምረውበት በግጭት ውስጥ የሚገኙትን አካላት ለማስማማት በተለያየ ዙር የተደረጉ ድርድሮች ፍሬያማ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
የሀማስን ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም ዳግም እንዳያንሰራራ ሆኖ ካልወደመ ከጋዛ ለቅቄ አልወጣም በሚለው አቋማቸው የጸኑት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ከተለያዩ አካላት እየደረሰባቸው የሚገኘው ተቃዎሞ ሀሳባቸውን የሚያስለውጣቸው አይመስልም፡፡
ግጭቱ አሁን በሚገኝበት ሁኔታ ጋዛን ተሻግሮ ቀጠናዊ ግጭት ወደ መሆን እየተንደረደረ ሲሆን ኢራን እና ቀጠናዊ አጋሮቿ በጦርነቱ የሚያደርጉት ተሳትፎም ከፍ እያለ መጥቷል፡፡
የየመኑ ሀውቲ ፣ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እንዲሁም በኢራቅ እና ሶርያ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ከእስራኤል ጋር ውጥረት ውስጥ ከሚገኙ የቀጠናው ተዋንያን መካከል ናቸው፡፡
አንድ አመት ባስቆጠረው የጋዛ ጦርነት እስራኤል በሰርጡ ውስጥ 40 ሺህ የሀማስ ኢላማዎች ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን 4700 የምድር ውስጥ ዋሻዎችን እና ከአንድ ሺህ በላይ የሮኬት ማስወንጨፍያ ጣብያዎችን አውድማለች፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሀይል የጥቅምት ሰባቱን ጥቃት አንደኛ አመት አስመልክቶ ባወጣው መረጃ፤ 726 ወታደሮቹ መገደላቸውን ሲያስታውቅ 380ዎቹ በጥቅምት 7 ጥቃት 346 ደግሞ በጋዛ ውስጥ በሚደረገው ውግያ መሞታቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
በጦርነቱ ከ4576 በላይ ወታደሮች ሲቆስሉ ጦሩ 300 ሺህ ለሚጠጉ ተጠባባቂ ጦር አባላት ጥሪ ያደረገ ሲሆን 82 በመቶዎቹ ወንዶች 18 በመቶዎቹ ደግሞ ከ20-29 እድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡
13200 ሮኬቶች ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ ከጋዛ ወደ እስራኤል ተተኩሰዋል፤ በተጨማሪም 12400 ከሊባኖስ ፣ 60 ከሶርያ ፣ 180 ከየመን እና 400 ሮኬቶች ከኢራን እንደተተኮሱበት ነው ጦሩ የገለጸው፡፡
እስራኤል በሊባኖስ በአንድ አመት ውስጥ በ4900 ኢላማዎች ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን 800 የሄዝቦላህ አባላትን ገድላለች ፡፡
እንደ እስራኤል መከላከያ ሀይል መረጃ ከሆነ በአንድ አመት ውስጥ 8 የሃማስ ታጣቂ ብርጌድ መሪዎች ሲገደሉ 30 የሺአለቃ መሪዎች 165 በተለያየ እርከን ላይ የሚገኙ ወታደራዊ አዛዦችን ገድላለች፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ከ40 ሺህ የሀማስ ታጣቂዎች መካከል ግማሽ ያህሉ መማረካቸውን እና መገደላቸውን እንዲሁም የቡድኑ 90 በመቶ ሮኬቶች መውደማቸው ተነግሯል፡፡