የዛሬው ልውውጥ ሶስት ታጋቾች በ90 ፍልስጤማውያን እስረኞች ከተለወጡበት ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ከሆነበት ከባለፈው እሁድ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ነው
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ በሁለት መቶ ፍልስጤማውያን እስረኞች የቀየራቸውን አራት የእስራኤል ሴት ታጋች ወታደሮች በቀይ መስቀል በኩል ለእስራኤል አስረክቧል።
አራቱ ታጋቾች በደርዘን በሚቆጠሩ የሀማስ ታጣቂዎች ተከበው በርካታ ነዋሪ በተገኘበት በጋዛ ከተማ ወደ መድረክ ሲወጡ ታይተዋል። ታጋቾቹ ወደ ቀይመስቀል መኪና ከመግባታቸው እና የእስራኤል ኃይል ወደአለበት ቦታ ከመውሰዳቸው በፊት እጃቸውንም አውለብልበዋል፤ ፈገግታም አሳይተዋል።
የዛሬው ልውውጥ ሶስት ታጋቾች በ90 ፍልስጤማውያን እስረኞች ከተለወጡበት ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ከሆነበት ከባለፈው እሁድ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ነው።
የእስራኤል ጦር አራቱን ታጋቾች በጋዛ መቀበሉን ገልጿል።
አራቱ ታጋች ወታደሮች እንዲለቀቁ እስራኤል 200 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ከእስር ቤት ለቃለች።
የተለቀቀት አራቱ ወታደሮች ማለትም ካሪና አሪቭ፣ ዳኒኤላ ጊልባኦ፣ናአሜ ለቪይ እና ሊሪ አልባግ ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 በደቡብ እስራኤል ድንበር ጥሶ ጥቃት በከፈተበት ወቅት ጋዛ ጫፍ አካባቢ በሚገኝ ወታደራዊ ሰፈር በቅኝ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ናቸው።
ስድስት ሳምንት በሚወስደው የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ በተለቀቁ በእያንዳንዳቸው ሴት ወታደሮች 50 ፍልስጤማውያን ለመፍታት መስማማቷን ባለስልጣናት ተናግረዋል። ይህ ማለት በአራት ወታደሮች ምትክ 200 ፍልስጤማውያን ይለቀቃሉ ማለት ነው።
እስራኤል ባለፈው እሁድ ሮሚ ጎኔን፣ ኢምሊ ደማሪና ዶሮን ስቴንብሬቸር ከተለቀቁና ለአስርት አመታት የጠፋው የእስራኤል ወታደር አስከሬን ከተገኘ በኋላ 94 እስራኤላውያንና የውጭ ዜጎች በጋዛ ተይዘው እንደሚገኙ ገልጻለች።
በግብጽና ኳታር የተመራውና ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ለወራት በተካሄደው ድርድር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በህዳር 2023 ለአንድ ሳምንት ከቆየው ተኩስ ጋብ የማድረግ ስምምነት ወዲህ ውጊያውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስቆመ ነው።
በመጀመሪያው ዙር ሀማስ 33 ተሟጋቾችን በእስራኤል እስርቤቶች ታሰረው የሚገኙ በመቶዎች በሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ለመለወጥ ተስማምቷል። በሁለተኛው ዙር ሁለቱ ወገኞች የቀሩ ታጋቿች በሚለቀቁበትና የእስራኤል ጦር ለ15 ወራት በዘለቀው ጦርነት በአብዛኛው ከፈራረሰችው ከጋዛ በሚወጣበት ሁኔታ ይደራደራሉ።
ሀማስ በጥቅምት 7፣ 2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት በመክፈት 1200 ሰዎችን መግደሉን እና 250 ሰዎችን አግቶ መወሰዱን ተከትሎ እስራኤል በከፈተችው ዘመቻ 47ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።