ሀማስ በሁለተኛው ዙር የሚለቀቁ የእስራኤል ታጋቾችን ይፋ አደረገ
የእስራኤል የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ሆስፒታሎች ታጋቾችን ለመቀበል እየተጠባበቁ ነው።
የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ በሆነበት በመጀመሪያው ቀን ባለፈው እሁድ ሶስት የእስራኤል ሴት ታጋቾች በ90 ፍልስጤማውያን እስረኞች ተለውጠዋል
ሀማስ በሁለተኛው ዙር የሚለቀቁ የእስራኤል ታጋቾችን ይፋ አደረገ።
ሀማስ ከእስራኤል ጋር በደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት በሁለተኛ ዙር በፋልስጤማውያን እስረኞች የሚለወጡ አራት የታገቱ ሴት የእስራኤል ወታደሮችን እንደሚለቅ አስታውቋል።
ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 በደቡብ እስራኤል ጥቃት በከፈተበት ወቅት ጋዛ አቅራቢያ የእስራኤል ጦር የቅኝት አባላት የነበሩት ካሪና አሪቭ፣ ዳኒኤላ ጊልባኦ፣ናአሜ ለቪይ እና ሊሪ አልባግ ዛሬ እንደሚለቀቁ ቡድኑ ገልጿል።
ይህ ልውውጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ በሆነበት የመጀመሪያው ቀን ባለፈው እሁድ ሶስት የእስራኤል ሴት ታጋቾች በ90 ፍልስጤማውያን እስረኞች መለወጣቸውን ተከትሎ የሚካሄድ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ቢሮ ባለፈው አርብ እለት የሚለቀቁት ታጋቾች ዝርዝር እንደደረሰው ያረጋገጠ ቢሆንም ስሞችን ይፋ አለማድረግን መርጧል። ቢሮው ባወጣው መግለጫ እስራኤል ቆይታ ምላሽ እንደምትሰጥ ነበር የገለጸው።
ሮይተርስ የእስራኤል መገናኛ ብዙኻንን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ዝርዝሩ የወጣው ሀማስ እና እስራኤል መጀመሪያ በደረሱት ስምምነት መሰረት አይደለም። ሲቪል የሆነው አርቤል የሁድ በዝርዝሩ መሰረት ይለቀቃል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
የእስራኤል የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ሆስፒታሎች ታጋቾችን ለመቀበል እየተጠባበቁ ነው።
ዛሬ እንደሚለቀቁ የሚጠበቁትና ሌላ አንድ ወታደር ከናሀል ኦዝ ወታደራዊ ሰፈር ከተያዙ በኋላ የሚያሳይ ቪዲዮ በእስራኤል ቴሌቪዥን ባለፈው አመት ተላልፎ ነበር። ቤተሰቦቻቸው ቪዲዮው በቴሌቪዥን እንዲተላለፍ የፈቀዱት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ታጋቾች እንዲመለሱ ጫና ለመፍጠር ነበር።
ስድስት ሳምንት በሚወስደው የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ በተለቀቁ በእያንዳንዳቸው ሴት ወታደሮች 50 ፍልስጤማውያን ለመፍታት መስማማቷን ባለስልጣናት ተናግረዋል። ይህ ማለት በአራት ወታደሮች ምትክ 200 ፍልስጤማውያን ይለቀቃሉ ማለት ነው።
የሀማስ የእስረኞች ሚዲያ ቢሮ እንደገለጸው ዛሬ የሚለቀቁ የ200 እስረኞችን ስም ዝርዝር እየጠበቀ መሆኑን በትናንትናው እለት አስታውቋል። ዝርዝሩ 120 የእድሜ ልክ ጽኑ እስራትና 80 የረጅም ጊዜ እስራት የተፈረደባቸውን ያካትታል ብሏል ሀማስ።
እስራኤል ባለፈው እሁድ ሮሚ ጎኔን፣ ኢምሊ ደማሪና ዶሮን ስቴንብሬቸር ከተለቀቁና ለአስርት አመታት የጠፋው የእስራኤል ወታደር አስከሬን ከተገኘ በኋላ 94 እስራኤላውያንና የውጭ ዜጎች በጋዛ ተይዘው እንደሚገኙ ገልጻለች።
በግብጽና ኳታር የተመራውና ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ለወራት በተካሄደው ድርድር የተደረሰው ተኩስ አቁም ስምምነት በህዳር 2023 ለአንድ ሳምንት ከቆየው ተኩስ ጋብ የማድረግ ስምምነት ወዲህ ውጊያውን ለመጀመሪያ ጊዜ አስቁሞታል።
በመጀመሪያው ዙር ሀማስ 33 ተሟጋቾችን በእስራኤል እስርቤቶች ታሰረው የሚገኙ በመቶዎች በሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ለመለወጥ ተስማምቷል። በሁለተኛው ዙር ሁለቱ ወገኞች የቀሩ ታጋቿች በሚለቀቁበትና የእስራኤል ጦር ለ15 ወራት በዘለቀው ጦርነት በአብዛኛው ከፈራረሰችው ከጋዛ በሚወጣበት ሁኔታ ይደራደራሉ።
ሀማስ በጥቅምት 7፣ 2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት በመክፈት 1200 ሰዎችን መግደሉን እና 250 ሰዎችን አግቶ መወሰዱን ተከትሎ እስራኤል በከፈተችው ዘመቻ 47ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።