ዶናልድ ትራምፕ የጆን ኤፍ ኬኔዲ እና ማርቲን ሉተር ኪንግ ግድያን የተመለከቱ ሚስጥራዊ ሰነዶች ለህዝብ ይፋ እንዲሆኑ አዘዙ
በአሜሪካ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሰዎች ግድያ ለአስርተ አመታት ሚስጥራዊ ሆኖ ቆይቷል
ፕሬዝዳንቱ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ይህን እና ሌሎች ሚስጥራዊ ሰነዶችን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙ ሶስት አነጋጋሪ እና ሚስጥራዊ ግድያዎች ይፋ እንዲደረጉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
ትራምፕ የፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ (ጄ ኤፍ ኬ)፣ የወንድማቸው ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ እና ከማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ግድያ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ባለስልጣኖች እቅድ እንዲያወጡ አዘዋል፡፡
ትዕዛዙ ከፍተኛ የአስተዳደሩ ባለስልጣናት በ15 ቀናት ውስጥ ሰነዶችን በመለየት በምን አይነት መንገድ ይፋ እንደሚደረጉ እቅድ እንዲያቀርቡ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
ትራምፕ ሰሞኑን ሰነዶቹን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር “ብዙ ሰዎች ይህንን ለማወቅ ለአስርተ ዓመታት እየጠበቁ ናቸው፤ በቅርቡ ሁሉም ነገር ይገለጣል" ብለዋል፡፡
ፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በዳላስ ቴክሳስ በ1963 ተገደሉ ፣ወንድማቸው ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ በካሊፎርኒያ 1968 ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ተገድለዋል። ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ በአሜሪካ ታዋቂው የሲቪል መብቶች ተከራካሪ ማርቲን ሉተር ኪንግ በሜምፊስ ቴነሲ መገደሉ ይታወሳል፡፡
ከምርመራዎቹ ጋር የተያያዙት ብዙዎቹ ሰነዶች ከግድያው በኋላ ይፋ ቢደረጉም በተለይ ከጄ ኤፍ ኬ ግድያ ጋር የተያያዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶች ከህዝብ አይን እና ጆሮ ተከልለው ሚስጥር ሆነው ቆይተዋል፡፡
ፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ወደ ሶቭየት ዩኒየን ከድቶ ወደ አሜሪካ በተመለሰው የቀድሞ የባህር ሀይል አባል ሊ ሃርቪ ኦስዋልድ በጥይት ተመተው መገደላቸውን እና ኦስዋልድ ድርጊቱን ብቻውን እንደፈጸመው የመንግስት የምርመራ ኮሚሽን ከአመታት በፊት ይፋ አድረጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ይፋ በሆነው መረጃ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች መኖር ከግድያው ጀርባ የመንግስት ሰላዮች ፣ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች (ማፍያዎች) እና ሌሎችም አካላት እጃቸው እንዳለበት የሚናገሩ አማራጭ የሴራ ትንታኔዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡
ለብዙ አሥርተ ዓመታት ከህዝብ የተሰበሰበው አስተያየት እንደሚያመለክተው በርካታ አሜሪካውያን የጄ ኤፍ ኬ ብቸኛው ገዳይ ኦስዋልድ ነው ብለው አያምኑም።
በአሜሪካ ፖለቲካ እና በመላው ጥቁሮች ዘንድ እንደ ጀግና የሚታየው የነጻነት እና መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ በነጭ ብሔርተኛ እንደተገደለ ቢነገርም፤ ገዳዩ ከጀርባው በርካታ እጆች እንዳሉ የሚያምኑ ደጋፊዎቹ እና ወዳጆቹ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
ትራምፕ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ሁሉንም ሰነዶች ይፋ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር፤ ነገር ግን የሲአይኤ እና የኤፍቢአይ ባለስልጣናት አንዳንድ ፋይሎችን በሚስጥር እንዲይዙ ካግባቧቸው በኋላ የገቡትን ቃል ሳይጠበቁ ቀርተዋል፡፡
በአዲሱ አስተዳደራቸው ሰነዶቹ ይፋ እንዲደረጉ በፈረሙት የስራ የአስፈፃሚ ትዕዛዝ የሰነዶቹ ሚስጥራዊ ሆኖ መቀጠል "ከህዝብ ጥቅም ጋር የማይጣጣም" ነው ሲል አስቀምጧል፡፡
ሆኖም አሁንም የተለያዩ የስለላ እና የደህንነት ድርጅቶች ሁሉም ሰነዶች ይፋ እንዳይደረጉ በመጠየቅ ላይ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡