እስራኤል ጦርነቱን የምታቆም ከሆነ "ሙሉ ስምምነት" ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ሀማስ ገለጸ
ሀማስ ይህን መግለጫ ያወጣው እስራኤል የተመድ ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ ወደ ጎን ትታ በደቡባዊ ጋዛ እያካሄደች ያለውን ጥቃት ባጠናከረችበት ወቅት ነው
ሀማስ ጦርነቱ እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ በተጨማሪ ድርድሮች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላው ለአደራዳሪዎቹ በትናንትናው እለት ገልጿል
ሀማስ ጦርነቱ እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ በተጨማሪ ድርድሮች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላው ለአደራዳሪዎቹ በትናንትናው እለት ገልጿል።
ነገርግን ሀማስ እንደገለጸው እስራኤል ጦርነቱን የምታቆም ከሆነ ግን ታጋቾችን በእስረኞች መለወጥን ጨምሮ "ሙሉ ስምምነት" ለማድረግ ዝግጁ ነው።
በግብጽ እና በኳታር አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው የእስራኤል እና የሀማስ የተኩስ አቁም ድርድር እንዳቸው ሌላኛቸው ያቀረቡትን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ በማድረጋቸው እስካሁን አልተሳካም።
ሀማስ ይህን መግለጫ ያወጣው እስራኤል የተመድ ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ ወደ ጎን ትታ በደቡባዊ ጋዛ እያካሄደች ያለውን ጥቃት ባጠናከረችበት ወቅት ነው።
"ሀማስ እና የፍልስጤም ኃይሎች ወረራ፣ ከበባ እና የዘርማጥፋት እየተካሄደ ባለበት ወቅት የተኩስ አቁም ድርድር ላይ አንሳተፍም" ብሏል ሀማስ ባወጣው መግለጫ።
ጦርነት በመሸሽ ከ2.3 ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪ ግማሽ ያህል የተጠለሉባትን ራፋ እንዳታጠቃ አለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት(አይሲጄ) ውሳኔ ያሳለፈ ቢሆንም እስራአል እያደረሰች ያለውን ከባድ የተባለ ጥቃት ቀጥላበታለች።
የእስራኤል ጦር በፈጸመው ጥቃት በጋዛ እና በግብጽ መካከል ያለውን የፊላደልፊን መተላለፊያ ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሯል።
"የፊላደልፊ ኮሪደር( መተላለፊያ) በተደጋጋሚ የጦር መሳሪያ ለማስገባት ለሚጠቀምበት ሀማስ እንደዋና የህይወት አስትንፋስ ሲያገለግል ነበር" ብለዋል ሀጋሪ።
ቃል አቀባዩ እንደተናገሩት አሁን ላይ በፊላደልፊ መተላለፊያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን እየተቆጣጠረ ያለው የእስራኤል ጦር ነው።
ጋዛን ከግብጽ ጋር የሚያገናኘውን የየብስ መተላለፊያ እስራኤል እስካሁን በቀጥታ ሳትቆጣጠረው ቆይታለች።
የእስራኤል ታንኮች በትናንትናው እለት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ራፋ መሀል ከተማ ሰንጥቀው ገብተዋል።እስራኤል ራፋን ለማጥቃት የወሰነችው የሀማስ የመጨረሻ ምሽግ ይገኝባታል በሚል መሆኑን መግለጿ ይታወሳል።
አይሲጄ በውሳኔው ሀማስ ያለቅድመ ሁኔታ ያገታቸውን እንዲለቅ ጥሪ አቅርቦም ነበር።
እስራኤል፣ ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ድንበር በመጣስ ከባድ የተባለ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ እየፈጸመች ባለው ጥቃት እስካሁን 36ሺ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።