እስራኤል በራፋ የፈጸመችው የአየር ጥቃት አለም አቀፍ ቁጣን ቀሰቀሰ
በጥቃቱ እስካሁን 45 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ ግማሽ ያህሉ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸው ታውቋል
ጥቃቱን ተከትሎ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ የሞቱ ፍልስጤማዊያን ቁጥር ከ36ሺህ ተሻግሯል
እስራኤል ትላንት ምሽት በራፋ የፈጸመችው የአየር ጥቃት የበርካታ ንጹሀንን ህይወት መቅጠፉን ተከትሎ አለም አቀፍ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡
ከጦርነት ነጻ በተባለው በአብዛኛው ተፈናቀዮች በሚገኙበት በራፋ ግዛት በተፈጸመው የአየር ጥቃት ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው ድንኳኖች ላይ በፈጠረው ቃጠሎ ምክንያት ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ የ45 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
ይህን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ቁጣቸውን የገለጹ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ የተለያዩ የአለም ሀገራት መሪዎች አለም አቀፉ ፍርድ ቤት እስራኤል ጦርነቱን እንድታቆም ትዕዛዝ እንዲያወጣ ጠይቀዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኤክስ ገጻቸው በእስራኤል ጥቃት መቆጣታቸውን ገልጸው ‘’በራፋ ለንጹሀን መከለያ የሚሆን ምንም አይነት ስፍራ አልተረፈም፣ ይህ ሀላፊነት የጎደለው ጥቃት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል’’ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፍ ቦሬል የአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊከበር ይገባል፣ አለም አቀፍ የሰበአዊ ህጎች በሁሉም ቦታ ተግባራዊ ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የአየርላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሚካኤል ማርቲን በበኩላቸው ‘’ከረሀብ እና ከበቂ የመድሀኒት አገልግሎት ውጭ በሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸመው የአየር ጥቃት አረመኔያዊ ነው’’ ሲሉ ገልጸውታል
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ በታንክ እያደረገው የሚገኝው የታንክ ድብደባ የቀጠለ ሲሆን በዛሬው እለት ተጨማሪ 8 ሰዎች መገደላቸውን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
የእስራኤል ጦር በበኩሉ የእሁዱ የአየር ጥቃት በተጠና መረጃ ተመርኩዞ በሀማስ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው ሲል ድርጊቱን አስተባብሏል፡፡
ከራፋህ ግዛት የተተኮሱ 8 ሮኬቶችን አክሽፌያለሁ ያለው ጦሩ የአየር ጥቃቱ ለዚህ የተሰጠ ምላሽ ነው ነው ያለው፡፡
ይሁንና መረጃዎች ጥቃቱ የተፈጸመው በምስራቅ ራፋ በርካታ ተፈናቃዮች በሚገኙበት ‘’ቴል አል ሱልጣን’’ መንደር የተካሄደ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የአካባቢው የጤና ሃላፊዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተናግረው የአየር ጥቃቱን ተከትሎ በተፈጠረ ከፍተኛ ቃጠሎ ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
የራፋ ሆስፒታል እና በስፍራው የሚገኝው የቀይ መስቀል ተንቀሳቃሽ ሆስፒታሎች በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማስተናገድ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ በሰሜናዊ ጋዛ ወደ ሚገኝው ካሃን የኑስ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡
ኳታር፣ ግብጽ እና ሳኡዲ አረብያ በትላንቱ የአየር ጥቃት ላይ ቁጣቸውን ከገለጹ ሀገራት መካከከል ናቸው ፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባሳለፍነው አርብ እስራኤል በጋዛ የምታደረገውን ወታደራዊ ዘመቻ እንድታቆም ትዕዛዝ ቢያሳልፍም ቴልአቪቭ በጥቃቷ ቀጥላለች፡፡