እስራኤል ጋዛን ከግብጽ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሯን አስታወቀች
14 ኪሎሜትር የሚረዝመው “የፊላደልፊ መተላለፊያ የሃማስ ኦክስጂን ነበር” ብለዋል የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳኔል ሃጋሪ
እስራኤል ሃማስ በዋሻዎች የጦር መሳሪያ አስርጎ ያስገባበታል ያለችውን መተላለፊያ የተቆጣጠረችው በራፋህ የጀመረችው ዘመቻ ቅቡልነት እንዲኖረው ለማድረግ ነው ተብሏል
እስራኤል ጋዛን ከግብጽ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሯን አስታወቀች።
ደቡባዊ ጋዛን ከግብጽ ጋር የሚያዋስነውና እስራኤል “ፊላደልፊ ኮሪደር” እያለች የምትጠራው መተላለፊያ እስራኤል ያልተቆጣጠረችው ብቸኛ የጋዛ ሰርጥ የየብስ ድንበር ነበር።
14 ኪሎሜትር የሚረዝመው መተላለፊያ በእስራኤል ጦር በቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ ጋዛ ምንም አይነት የየብስ ድንበር አይኖራትም።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳኔል ሃጋሪ “የፊለደልፊ መተላለፊያ ለሃማስ የህይወት መስመሩ ወይም ኦክስጅኑ ሆኑ ቆይቷል፤ ቡድኑ በዚህ መስመር ነበር የጦር መሳሪያዎችን ወደ ጋዛ ሰርጥ የሚያስገባው” ብለዋል።
የእስራኤል ጦር መተላለፊያውን ሲቆጣጠር ሃማስ ወደ ጋዛ የጦር መሳሪያ ሲያስገባባቸው የነበሩ 20 የሚጠጉ ዋሻዎች መገኘታቸውንም ቃል አቀባዩ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር ኮሪደሩን ተቆጣጥሬ የጦር መሳሪያ ማሻገሪያ ዋሻዎችን አግኝቻለሁ የሚለው መግለጫው ከግብጽ ባለስልጣናት ተቃውሞ ገጥሞታል።
ከግብጽ ወደ ጋዛ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዳይኖር ድንበር ተሻጋሪ ዋሻዎችን ማውደሟን ስትገልጽ የቆየችው ካይሮ፥ የቴል አቪቭ አዲስ ክስ በራፋህ የጀመረችው ዘመቻ ቅቡልነት እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ ነው ማለቷን የሀገሪቱን መገናኛ ብዙሃን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።
የአለማቀፉ ፍርድቤት ትዕዛዝን ወደ ጎን በመተው ወደ ራፋህ የዘለቀችው እስራኤል በማዕከላዊ የከተማዋ ክፍሎች ታንኮች ጭምር ገብተው ውጊያው መቀጠሉን የአይን እማኞች ተናግረዋል።
የእስራኤል የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ዛቺ ሄኒቢ የጋዛው ጦርነት ቢያንስ እስከ 2024 መጨረሻ ይቆያል የሚል አስተያየት መስጠታቸውም ሀገሪቱ ጦርነቱ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላት ያሳያል ተብሏል።
እስራኤል የራፋህ ዘመቻውን ከጀመረች ወዲህ ታጋቾችን ዘንግታቸዋለች የሚሉ የታጋች ቤተሰቦች አሁንም የኔታንያሁ አስተዳደር ወደ ተኩስ አቁም ድርድሩ እንዲመለስ ቢጠይቁም ሰሚ ያጋኙ አይመስሉም።
በራፋህ ወረራ ከተፈጸመ የጦር መሳሪያ ድጋፌን አቋርጣለሁ ስትል የቆየችው አሜሪካም “እስካሁን ቀይ መስመሬ አልተነካም” የሚል መግለጫ መስጠቷ ኔታንያሁን “ግፋበት” እንደማለት ተቆጥሯል።
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ (አልቃሳም ብርጌድ) እና ኢስላሚክ ጂሃድ ቡድን በበኩላቸው እስራኤል በራፋህ ድብደባዋን እስካላቆመች ድረስ የተኩስ አቁም ንግግር ማድረጉ እርባናቢስ ነው፤ ትግል ብቸኛው አማራጭ ነው ብለው በራፋህ ውጊያው ቀጥሏል።