እስራኤል አለምአቀፍ አደራዳሪዎቹ ያቀረቡትን እቅድ ውድቅ ማድረጓን ተከትሎ የጋዛ ተኩስ አቁም ጥረቶች ወደ ዜሮ መመለሱን ሀማስ ገልጿል
እስራኤል አለምአቀፍ አደራዳሪዎቹ ያቀረቡትን እቅድ ውድቅ ማድረጓን ተከትሎ የጋዛ ተኩስ አቁም ጥረቶች ወደ ዜሮ መመለሱን የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ በትናትናው እለት ገልጿል።
ኃይት ሀውስ ሁለት አካላት ንግግራቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየጣርኩ ነው ብሏል።
- የእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር የጦር የመሳሪያ ድጋፍ ከቆመ “በጥፍራችንም ቢሆን እንዋጋለን” አሉ
- የእስራኤል ዋነኛ የጦር መሳሪያ አቅራቢዎች እነማን ናቸው?፤ የትኞቹስ ማቅረባቸውን አቆሙ?
ሀማስ ባወጣው መግለጫ ባለፈዉ ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ባደረሰው ከባድ ጥቃት ምክንያት የተቀሰቀሰው ሰባት ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት የሚቆምበትን ዘዴ ለመንደፍ ከሌሎች የፍልስጤም ታጣቃዎች ጋር እንደሚመክር አሳውቋል።
ተመድ ከሰአታት ቀደም ብሎ እስራኤል በዚህ ሳምንት ለፍልስጤማውያን እርዳታ ለማድረስ ወሳኝ የሆነውን በጋዛ እና በግብጽ መካከል ያለውን የራፋ ማቋረጫ በመቆጣጠሯ ወደ ጋዛ የሚሄደው እርዳታ ሊቆም ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
እስራኤል የአሜሪካን ጫና ወደ ጎን በመተው፣ ጦርነት ሸሽተው የተፈናቀሉ አንድ ሚሊዮን ሰዎች የተጠለሉባትን እና እስራኤል የመጨረሻው የሀማስ ምሽግ ይገኝባታል የምትላትን ራፋን ማጥቃቷን ቀጥላበታለች።
እስራኤል በአሁኑ ወቅት ምስራቅ እና ምዕራብ ራፋን የሚያገናኘውን ዋና መንገድ በመቆጣጣር ምስራቃዊ የከተማዋን ክፍል ሙሉ በሙሉ ከበባ ውስጥ እስገብታለቸ። በዚህ ምክንያት አሜሪካ ለእስራኤል ልትጭነው የነበረውን የጦር መሳሪያ አቁማለች።
"እስራኤል ማቋረጫውን ለሰብአዊ እርዳታ ክፍት አንድታደርገው በድጋሚ እንጠይቃለን" ሲሉ የኃይት ሀውስ የብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ክርቢይ ተናግረዋል።
የእስራኤል ራፋን የማጥቃት እቅድ ከዋነኛ አጋሯ ጋር ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።
ሀማስ፣ ግብጽ እና ኳታር ያቀረቡትን ሶስት ምዕራፍ ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምቶ ነበር።ነገርግን እስራኤል ቅድመ ሁኔታዎች በትክክል አልተሟሉም በማለት ውደቅ አድርጋዋለች።