አሜሪካ ለእስራኤል በሰጠቻቸው ቦምቦች ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን አመነች
የእስራኤል ጦር ወደ ራፋህ ገብቶ ጥቃት ከከፈተ ቀጣይ እርምጃዎችን እወስዳለሁ ስትልም አስጠንቅቃለች
እስራኤል በበኩሏ ወደ በራፋህ አዲስ ጥቃት ማድረስ ጀምራለች
አሜሪካ ለእስራኤል በሰጠቻቸው ቦምቦች ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን አመነች።
ለፍልስጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር ጦርነት የተቀሰቀሰው።
እስራኤል በሐማስ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ጥቃት ባለችው የመልሶ ማጥቃት ከ34 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ " ለእስራኤል በሰጠነው ቦምብ ንጹሀን ተገድለዋል" ብለዋል።
"ወደ እስራኤል ቦምብ አንልክም" ያሉት ፕሬዝዳንቱ እስራኤል ወደ ራፋህ ጦሯን እንዳትልክ እና ንጹሀንን እንዳትጎዳ ለጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መናገራቸውንም ጠቅሰዋል።
እስራኤል ጦሯን በርካታ ስደተኞች ወደ ተጠለሉበት ራፋህ ከላከች ተጨማሪ እርምጃዎች ሊወሰድ ይችላል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ በቃለ መጠይቃቸው ላይ ተናግረዋል።
ይሁንና የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሐማስ ታጣቂዎች በራፋህ እንደሚገኙ እና እነሱን ለመደምሰስ ጦራቸው ወደ ራፋህ መግባቱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ወደ ራፋህ እንዳንገባ የሚከለክለን አካል የለም ያሉ ሲሆን ስለ አሜሪካ አዲስ ውሳኔ እስካሁን በይፋ ከመናገር ተቆጥበዋል።
በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኤርዳን የአሜሪካ ውሳኔ የሚያበሳጭ ነው ያሉ ሲሆን ዋሸንግተን ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ ማቆም የለባትም ብለዋል።
ከአሜሪካ በተጨማሪም ካናዳ እና ሌሎችም የአውሮፓ ሀገራት ለእስራኤል የጦር መሳሪያ እንዳይሸጥ እገዳ ጥለዋል።
እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ለማድረግ፣ ታጋቾችን ለመልቀቅ እና ሌሎችንም ጉዳዮች ለመመለስ በሚል የሰላም ስምምነት ለመፈራረም የተስማሙ ቢሆንም አዲሱ የራፋህ ጥቃት ስምምነቱ እንዲፈርስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።