ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጦሩ እንዲንቀሳቀስ አዘዋል
የጋዛ ሰርጥ የሚያስተዳድረው ሀማስ ያልተጠበቀና በተለያየ አቅጣጫ የተቃጣ ጥቃት እስራኤል ላይ አድርሷል።
በሽህዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን በማዝነብ ታጣቂዎቹ ጠንካራውን ድንበር በመስበር ሰርገው እንደገቡ ተነግሯል።
በአየር፣ በምድርና በባህር በተለያዩ አቅጣጫዎች የተሰነዘረው ጥቃቱ እስራእል ሳትጠበቀው የተፈጸመባት ነው ተብሏል።
ወረራዉ ከተጀመረ ከስድስት ሰዓታት በኋላ የሀማስ ታጣቂዎች በበርካታ የእስራኤል ማህበረሰቦች ውስጥ እየተኮሱ መሆኑን መገናኛ ብዙኸን ዘግበዋል።
ጥቃቱ ሀገሪቱን ያናወጠ መሆኑንም ተነግሯል።
የእስራኤል ብሄራዊ የነፍስ አድን አገልግሎት ቢያንስ 22 ሰዎች መሞታቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን አስታውቋል።
ይህም በእስራኤል ባለፉት ዓመታት ከተፈጸሙ ጥቃቶች አስከፊው ነው ብሏል።
የሟቾቹ ቁጥር እስካሁን በይፋ ባይገለጽም የአሶሺየትድ ፕረስ ዘጋቢ የ15 ሰዎች ስርዓተ ቀብር መፈጸም መመልከቱን ተናግሯል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በቴሌቪዥን ቀርበው "ጦርነት ላይ ነን" ሲሉ አውጀዋል።
"ተልዕኮ አይደለም፣ ዙር አይደለም። ጦርነት ነው" ሲሉ የሀገሪቱ ጦር በስፋት እንዲንቀሳቀስ አዘዋል።