እስራኤል ጦሯን ከዌስትባንኳ ጀኒን ማስወጣት ጀመረች
በሁለት ቀናቱ ዘመቻ 13 ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
እስራኤል በሁለት አስርት አመታት ከፍተኛ ነው የተባለውን ዘመቻ በጀኒን ፈጽማለች
የእስራኤል ጦር በጀኒን ከተማ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ዘመቻ አጠናቆ ከከተማዋ መውጣት መጀመሩን አስታውቋል።
ቴልአቪቭ በከተማዋ በሚገኝ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ መሽገዋል ባለቻቸው የታጠቁ ሃይሎች ላይ የከፈተችው ጥቃት በአይነቱ የተለየ መሆኑ ተነግሯል።
በአየር ሃይል እና በእግረኛ ጦር በተካሄደው ዘመቻ 13 ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን፥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጀኒን ከተማ አቅራቢያ የወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያን ሲጎበኙ፥ “የሁለት ቀናቱ ዘመቻ ቢጠናቀቅም በቀጣይም ሽብርተኝነትን ለማጥፋት የሚወሰደው እርምጃ ይቀጥላል” ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
እስራኤል በዌስባንኳ ከተማ ጀኒን ለሁለት ቀናት ያካሄደችው ዘመቻ የፍልስጤም የታጠቁ ሃይሎች በእስራኤል ላይ ነፍጥ ካነሱ ወዲህ እጅግ ጠንካራው እንደነበር ተገልጿል።
ጋዛን የሚያስተዳድረው ሃማስ ለጀኒኑ ጥቃት አጻፋውን እንደሚመልስ ዝቷል።
የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት ከወደ ጋዛ የተወነጨፉ አምስት ሮኬቶችን ማክሸፉን ነው ያስታወቀው።
በቴል አቪቭም አንድ ፍልስጤማዊ በከፈተው ተኩስ ሰባት እስራኤላውያን መቁሰላቸውን ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “እነዚህ ጥቃቶች በሽብርተኝነት ላይ የከፈትነውን ዘመቻ የሚያስቆሙ የሚመስላቸው አካላት ተሳስተዋል” ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ግን እስራኤል በጀኒን በርካታ ንጹሃን በሚገኙበት አካባቢ የፈጸመችውን የአየር ጥቃት ተቃውሟል።
በጥቃቱ ህጻናት ጭምር መገደላቸውንና መሰረተ ልማት መውደሙን በመጥቀስም ቴል አቪቭ የፍልስጤም ውጥረትን ከሚያባብስ ተግባር እንድትታቀብ ነው የጠየቀው።
የአለም ጤና ድርጅትም በጀኒን የስደተኞች ጣቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስቸኳይ ህክምና ለመስጠት አምቡላንሶቹ እንዳይገቡ መከልከሉን አስታውቋል።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በሁለት ቀናቱ ጥቃት ከ140 በላይ ፍልስጤማውያን መቁሰላቸውና 30ዎቹ በከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።