“ስካይ ሶኒክ” - የእስራኤል የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ጥቃት ጋሻ
ቴልአቪቭ “ፋታህ” የተሰኘውን የቴህራን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሳይቀር የሚያደባይ መቃወሚያ ሰርቻለሁ ብላለች
የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል መስፋፋት ለአለም ሰላም ስጋት ደቅኗል
ኢራን “ፋታህ” የሚል ስያሜ የሰጠችውን የመጀመሪያ ሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤሏን ካስተዋወቀች ከአንድ ሳምንት በላይ ተቆጥሯል።
“ፋታህ” የአሜሪካ እና እስራኤል የሚሳኤል መቃወሚያዎችን አልፎ ጥቃት ማድረስ እንደሚችልም ቴህራን በሀገር ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራችውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ስታስተዋውቅ መናገሯ አይዘነጋም።
እስራኤል በበኩሏ በትናንትናው እለት ”ፋታህ” ሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤልን የሚያደባይ መቃወሚያ ሰርቻለሁ ብላለች።
የመንግስት ንብረት የሆነው የመሳሪያ አምራች ኩባንያ ራፋኤል ያስተዋወቀው ጸረ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል “ስካይ ሶኒክ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።
“ስካይ ሶኒክ” የባለስቲክም ሆነ ክሩዝ ሚሳኤሎች ኢላማቸውን ሳይመቱ አየር ላይ ይበትናቸዋል ብለዋል የኩባንያው ስራ አስኪያጅ ዩቫል ስቴኒትዝ ከሬውተርስ ጋር ባደረጉት ቆይታ።
ስለ አዲሱ የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል መቃወሚያ ከአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) ጋር ተነጋግረንበታል ያሉት ስራ አስኪያጁ፥ “ስካይ ሶኒክ” መቼ ወደ ስራ እንደሚገባ ግን አልገለጹም።
ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ከድምጽ በአምስት እጥፍ የሚልቅ ፍጥነት አላቸው፤ ይህም ከእይታ ውጭ እንዲሆኑና ተመተው እንዳይወድቁ ያደርጋቸዋል።
ኢራን ከዘጠኝ ቀናት በፊት ያስተዋወቀችው “ፋታህ” ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልም በስአት 15 ሺህ ኪሎሜትር መምዘግዘግ እንደሚችል ነው የተነገረው።
ይህም የእስራኤል አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን መቃወሚያ ስርአት አልፎ ጥቃት እንዲያደርስ ያስችለዋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፥ ቴል አቪቭ ለ”ፋታህ”ም ተዘጋጅቸበታለሁ ብላለች።
እስራኤል አዲሱን ጸረ ሚሳኤል በቀጣዩ ሳምንት በፓሪስ በሚካሄደው አለማቀፍ ሁነት ላይ እንደምታስተዋውቀቅ ተገልጿል።
ሩሲያ፣ ቻይና፣ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ለሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤል ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰሩ መሆኑ ይነገራል።
እንደ ዩክሬን ባሉ ሀገራትም የሚሳኤሎች ጥቅም ላይ መዋል እየጨመረ መሄዱ ገበያውን እንዳሰፋለት የሚጠቅሰው የእስራኤሉ ራፋኤል፥ ቴክኖሎጂው እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ቢመጣም መፍትሄውም በእጃችን ነው ሲል “ስካይ ሶኒክ”ን በአብነት አንስቷል።