በእስራኤል ትናንት ግማሽ ሚሊየን ሰዎች ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ተነገረ
በጋዛ ስድስት ታጋቾች መገደላቸውን ተከትሎ በእየሩሳሌም፣ ቴል አቪቭና ሌሎች ከተሞች ከባድ ተቃውሞ ተቀስቅሷል
ሰልፈኞቹ የኔታንያሁ አስተዳደር ቀሪዎቹን 101 ታጋቾች እንዲያስለቅቅ ጠይቀዋል
በጋዛ ስድስት ታጋቾች መገደላቸውን ተከትሎ እስራኤላውያን ቁጣቸውን በአደባባይ እያሰሙ ነው።
የኔታንያሁ አስተዳደር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሶ ታጋቾችን ማስለቀቅ አልቻለም ያሉ 500 ሺህ የሚገመቱ ሰልፈኞች በቴል አቪቭ፣ እየሩሳሌምና ሌሎች ከተሞች ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ሰልፈኞቹ በእየሩሳሌም መንገድ ዘግተው በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መኖሪያ ቤት ዙሪያ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ውለዋል።
የቴል አቪቭ ጎዳናዎችም የሟቾቹን ታጋቾች ምስሎች በያዙ ሰልፈኞች ተሞልተው መዋላቸውን ነው ሬውተርስ ያስነበበው።
ሰልፈኞቹ የኔታንያሁ አስተዳደር ቀሪዎቹን 101 ታጋቾች ለማስለቀቅ በፍጥነት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርስ ጠይቀዋል።
የእስራኤል ሌበር ፓርቲ በዛሬው እለት ዜጎች ለተቃውሞ አደባባይ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።
ከኔታንያሁ ጋር ቃላት ሲለዋወጡ የቆዩት የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ያር ላፒድ በቴል አቪቭ የተካሄደው ሰልፍ ላይ በርካቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበው ነበር።
የእስራኤል ፖሊስ ሰልፈኞቹን በውሃ ለመበተን መሞከሩንና መንገድ መዝጋቱን የሚያሳዩ ምስሎች የወጡ ሲሆን፥ 29 ሰዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
የ11 ወራቱን ጦርነት እንዲያቆሙ ጫናው የበዛባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የስድስቱን ታጋቾች ገዳዮች ተጠያቂ የሆኑ አካላት በቁጥጥር ስር ካላዋለች እረፍት የላትም ብለዋል።
“የትኛውም ታጋቾችን የሚገድል አካል ስምምነት እንደማይፈልግ ግልጽ ነው” ማለታቸውንም የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሃማስ ግን ታጋቾቹ ለህልፈት የተዳረጉት የተኩስ አቁም ስምምነቱ በመዘግየቱ ነው ብሏል።
የቡድኑ ከፍተኛ አመራር ሳሚ አቡ ዙህሪ “ለእስራኤል ታጋቾች ግድያ ተጠያቂው ኔታንያሁ ነው፤ እስራኤላውያን ኔታንያሁን አልያም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ይምረጡ” ሲሉም ለሬውተርስ ተናግረዋል።
የታጋቾቹ ቤተሰቦች ያቋቋሙት ፎረምም ኔታንያሁ ሃላፊነቱን እንዲወስዱ እና በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ ቀሪዎቹ ታጋቾች እንዲለቀቁ ጥር አቅርቧል።