በሐማስ ታግተው ከነበሩት ውስጥ ስድስቱ መገደላቸውን ተከትሎ በእስራኤል ቁጣ አገርሽቷል
እስራኤላዊን ወደ አደባባዮች በመውጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ከሐማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ጠይቀዋል
በሐማስ ከታገቱ 250 እስራኤላዊያን መካከል 100ዎቹ እስካሁን በሐማስ እጅ ይገኛሉ
በሐማስ ታግተው ከነበሩት ውስጥ ስድስቱ መገደላቸውን ተከትሎ በእስራኤል ቁጣ አገርሽቷል፡፡
ከ11 ወራት በፊት ለፍልስጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱ ይታወሳል፡፡
በዚህ የሐማስ ጥቃት ከ1 ሺህ 200 በላይ እስራኤላዊያን ሲገደሉ 250 ያህሉ ደግሞ ታግተው ከተወሰዱት ውስጥ 100 ያህሉ አሁንም በሐማስ እጅ አሉ ተብሏል፡፡
እስራኤል የታገቱ ዜጎቿን ለማስለቀቅ እና ለደረሰባት ጥቃት ምላሽ በሚል በሰነዘረቻቸው ጥቃቶች ከ40 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊን ተገድለዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በዛሬው ዕለት በሐማስ ታግተው ከነበሩ እስራኤላዊያን መካከል ስድስት ዜጎች ተገድለው መገኘታቸው ተገልጿል፡፡
የእስራኤል ጦር በታገቱበት ስፍራ የተገደሉ ስድስት እስራኤላዊያን ዜጎችን አስከሬን መውሰዱን ተከትሎ በሀገሪቱ የህዝብ ቁጣ ዳግም አገርሽቷል፡፡
እስራኤላዊያን ከሐማስ ጋር ድርድር ተደርጎ የተኩስ አቁም እና የታገቱ ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ ፍላጎት ቢኖራቸውም እስካሁን ይህ ባለመሆኑ ዜጎች በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለይ ተቃውሞዎች በርትተዋል፡፡
ተቃውሞውን ያበረታው ደግሞ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስሩ ዮዓቭ ጋላንት በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ላይ የስራ ማቆም አድማ እና ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲደረግባቸው ጥሪ ማቅረባቸው መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህን ተከትሎም ወደ አደባባይ ለተቃውሞ የወጡ እስራኤላዊያን ዜጎች ጠቅላይ ሚኒስር ኔታንያሁ ከሐማስ ጋር እንዲደራደሩ እና የታገቱ እስራኤላዊያን በህይወት ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመጡ እየጠየቁ ናቸው፡፡
ሐማስ በበኩሉ ግድያው የዘገየው የተኩስ አቁም እና ድርድር ውጤት ነው ያለ ሲሆን አሁንም ከእስራኤል ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው በተገደሉ እስራኤላዊያን ማዘናቸውን ገልጸው ግድያውን የፈጸመው አካል ዋጋውን ያገኛል ሲሉ ዝተዋል፡፡