18 ስአት የፈጀው የሃምቡርግ አውሮፕላን ማረፊያ የአጋች ታጋች ድራማ
የ35 አመቱ ወጣት የ4 አመት ሴት ልጁን በተሽከርካሪ ውስጥ አሳፍሮ ወደ ቱርክ ሊጓዝ ወደነበር አውሮፕላን ተጠግቶ ቆሟል
ክስተቱ ከ286 በላይ በራራዎችን አስተጓጉሎ ከ18 ስአት በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል
በጀርመኗ ሃምቡርግ ከተማ የሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ያልተጠበቀ ክስተት አስተናግዷል።
የ35 አመቱ ወጣት የአራት አመት ሴት ልጁን አሳፍሮ ተሽከርካሪውን ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ ያስገባል።
ግለሰቡ የደህንነት አጥሮችን በመጣስ ተሽከርካሪውን አውሮፕላኖች ወደሚቆሙበት ስፍራም በመውሰድ ያቆማል።
ሁለት ጊዜ ወደ ሰማይ ጥይት የተኮሰው ግለሰቡ የሚቀጣጠሉ ጠርሙሶችንም ይወረውራል። ይህም ፈንጂዎችን ይዟል የሚል ጥርጣሬውን ያጎላዋል።
ተሽከርካሪውን መንገደኞችን አሳፍሮ ጉዞ ሊጀምር ወደተዘጋጀ የቱርክ አየርመንገድ አውሮፕላን አስጠግቶ ማቆሙም ከፍተኛ ስጋት በመፍጠሩ መንገደኞቹ ከአውሮፕላኑ እንዲወጡ ይደረጋል።
ግለሰቡ ከልጁ ጋር ወደ ቱርክ ለመጓዝ ነው ተሽከርካሪውን ወደ አውሮፕላኑ ያስጠጋው።
የሃምቡርግ ፖሊስ እንዳስታወቀው ግለሰቡ ከቀድሞ ሚስቱ ጋር በነበረው አለመግባባት ሴት ልጁን ይዞ ከጀርመን ለመውጣት በማሰብ ነው ድርጊቱን የፈጸመው።
የልጁ እናት ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠቷ እና በቁጥጥር ስር እንዲውል ማዘዣ በመውጣቱም የአውሮፕላን ማረፊያው የጸጥታ ሃይሎች ግለሰቡ ከተሽከርካሪው ወርዶ እጁን እንዲሰጥ ጥያቄ ያቀርቡለታል።
ቱርካዊ ዜግነት እንዳለው የተነገረለት ግለሰብ ለስአታት ካመነታ በኋላም በመጨረሻ እጁን ሰጥቶ የ18 ስአቱ የአጋች ታጋች ድራማ ተጠናቋል።
ክስተቱ ከሀምቡርግ የሚነሱ እና ወደ ሀምቡርግ የሚደረጉ በርካታ በረራዎች እንዲሰረዙ ምክንያት ሆኗል።
ግለሰቡ ባለፈው አመትም ሴት ልጁን ያለእናቷ ፈቃድ አስገድዶ ወደ ቱርክ መውሰዱና እናቷ ወደ ጀርመን መልሳ እንዳመጣቻት የሃምቡርግ ከንቲባ ፒተር ሸንስቸር ያወሳሉ።
በጀርመን አስቸጋሪ ህይወት እየመራ መሆኑን የሚናገረው ግለሰቡ በህጻናት ጠለፋ ተከሶ በቁጥጥር ስር ሊውል ሲልም ከትናንት በስቲያ የፈጸመው ሌላ የእገታ ድራማ ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍለው ይጠበቃል።
በቱርካዊው ወጣት የተፈጸመው ድርጊት በሀምቡርግ 286 በረራዎችን ያስተጓጎለ ሲሆን ከ34 ሺህ በላይ መንገደኞችም በትናንትናው እለት ከአውሮፕላን ማረፊያው መውጣታቸው ነው የተነገረው።