የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በሆንግ ኮንግ የገጠመው ምንድን ነው?
አየር መንገዱ ከበረራ ቁጥር ET608 አውሮፕላን ጋር በተያያዘ የተሰሩ ዘገባዎች ስህተት መሆናቸውን ገልጿል
በሆንግ ኮንግ እና አካባቢው የነበረው የአየር ንብረት በአውሮፕላኑ ላይ ያደረሰው አስተዋጽኦስ ምን ነበር?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ቁጥር ET608 የተመዘገበው አውሮፕላን ከሁለት ቀናት በፊት ከአዲስ አበባ በባንኮክ ታይላንድ በኩል አድርጎ ወደ ሆንግ ኮንግ የበረረ አውሮፕላኑን በሚመለከት የተለያዩ ይዘት ያላቸው ዘገባዎች መሰራታቸውን አስታውቋል።
አየር መንገዱ ለተሰሩ ዘገባዎች ማስተካከያ በሚል ባወጣው መግለጫ በሆንግ ኮንግ በነበረው ከባድ የአየር ንብረት ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ብቻ መብረሩን በርካታ ዘገባዎች መሰራታቸው ስህተት እንደሆነ ገልጿል።
አየር መንገዱ በበረራ ቁጥር ET608 የተመዘገበው አውሮፕላን በፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 1 2023 በተያዘለት ሰአት በሆንግ ኮንግ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም ማረፍ መቻሉን አስታውቋል።
ይህ አውሮፕላን በሆንግ ኮንግ አውሮፕላን ማረፊያ ለበረራ ምቹ ያልሆነው የአየር ጸባይ ከመከሰቱ በፊት በሰላም ማረፉን የገለጸው አየር መንገዱ ሚዲያዎች በረራው በሆንግ ኮንግ ከባድ አውሎ ነፋስ መካከል ማረፍ ማቻሉን የዘገቡበት ዘገባ ስህተት መሆኑን ገልጿል።
አውሮፕላኑ ከባንኮክ ተነስቶ ወደ ሆንግ ኮንግ አየር ማረፊያ ሲደርስ ሊኖር የሚችለው የአየር ሁኔታ ደህንነቱ የተጠበቀ እንደነበር ከነበረው የአየር ትንበያ መረዳቱን እና አዲስ አበባ ባለው ዋና ማዕከል በተደረገ ክትትል እና የመረጃ ልውውጥ መሰረት ያለ ምንም የተለየ አስቸጋሪ ሁኔታ ማረፉንም አስታውቋል።
በዚሁ መሰረትም የአየር ሁኔታው በተለመደው ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ እና ከሆንግ ኮንግ አየር ማረፊያ (ATC) ፍቃድ በመሰጠቱ በረራው እንዲቀጥል መደረጉንም አየር መንገዱ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
በረራው የቀጠለው አውሮፕላኑ ሆንግ ኮንግ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ከባድ አውሎ ነፋሱ እንደማይኖር የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃውን መሰረት በማድረግ መሆኑንም አየር መንገዱ ገልጿል።
ወደ ሆንግ ኮንግ ይደረግ የነበረው በረራ ከተጠናቀቀ በኋላ እና የአየር ንብረቱ መባባሱን ተከትሎ አውሮፕላን ማረፊያው ስራ ለበረራ ዝግ በመሆኑ የመልስ በረራ አውሮፕላን ቁጥር ET609 ለ24 ሰዓት መራዘሙን አስታውቋል።